Fana: At a Speed of Life!

የኦሬንጅ በይነ መረብ ማዕከል በኢትዮጵያ ተከፈተ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ጂ አይ ዜድ እና ኦሬንጅ የኦሬንጅ በይነ መረብ ማዕከልን በኢትዮጵያ ከፈቱ፡፡

ማዕከሉ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቃዊ አፍሪካ ሶስተኛውና ወጣቶችን በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ ለማሠልጠንና የተሻለ የሥራ ዕድል እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እና ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር የዲጂታል ክህሎትን የሚያጎለብትና ለልዩ ልዩ ፈጠራዎች የሚያነሳሳ የኦሬንጅ ዲጂታል ማዕከል ነው ተብሏል፡፡

በማዕከሉ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ እና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ተገኝተዋል።

በ500 ሜትር ስኩዌር ላይ ያረፈው ዲጂታል ማዕከል ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን አቅፎ በመያዝ በምሥራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ማዕከል ሲሆን፥ በሀገራት መካከል የሚኖረውን የዕውቀት እና የልምድ ልውውጥ በማጎልበት የወጣቶችን የሥራ ዕድል በቀላል እና በልዩ ልዩ አማራጮች እንደሚያዳብር ታምኖበታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሥራ ፈጠራን በማበረታታት ሀገራዊ የዲጂታል ሥነ ምህዳርን ያስተዋውቃልም ነው የተባለው፡፡

የኦሬንጅ ዲጂታል ማዕከል የኮዲንግ ማሠልጠኛ ማዕከላትን፣ ፋብሎ ሶሊዴር እና የስታርትአፕ አክስሌተር “ኦሬንጅ ፋብ” ስትራቴጂካዊ ፕሮግራሞችን በአንድ ማዕቀፍ ሥር ማቅረብ እንዲሁም የኦሬንጅ ቬንቸር አፍሪካ የመዋዕለ ንዋይ ድጋፍ የማመቻቸት አላማ ያለው ነው፡፡

ሁሉም ፕሮግራሞች ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡት ከክፍያ ነጻ ሲሆን ለሁሉም ሰው ዕድል የሚሰጡ እና ለወጣቶች የዲጂታል ሥልጠናን ያካተቱ ናቸው፡፡

በሥልጠናው የተግባር፣ የስታርት አፕ አክስለሬሽን እንዲሁም የሥራ ፈጠራ እና ኢንቨስትመንት ትግበራ ሥልጠናዎች 90 በመቶውን የሚሸፍኑ ይሆናል፡፡

ማእከሉ በቀጣይ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በክልሎች ስራ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል፡፡

በይስማው አደራው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.