Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ በማድረግ ክልሉን የግጭት ማእከል ለማድረግ የተደረገው ሙከራ መክሸፉ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 29 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ በማድረግ ክልሉን የግጭት ማእከል ለማድረግ የተደረገው ሙከራ መክሸፉ ተገለፀ።
 
የክልሉ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መንገድ በመዝጋት የክልሉ ህዝቦችን አለመረጋጋት ውስጥ ለመክተት የተደረጉ ሴራዎች አልተሳኩም ብለዋል ።
 
በክልሉ በሁሉም አከባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴም ቀጥሏል ነው ያሉት ።
 
ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ማግስት በክልሉ የተፈጠረውን የንብረት ውድመትና እና የሰው ህይወት መጥፋት ለፖለቲካ ትርፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሀይሎች ጥረት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።
 
የተከሰተውን ችግር ከብሄር ጋር በማገናኘት አንዱን በሌላኛው ለማስነሳት እየሰሩም ናቸው ብለዋል ።
 
የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ መንገድ በማዘጋት መደበኛ እንቅስቃሴዎች እንዲቋረጡ የሰሩት ሀይሎች ፤ በክልሉ ህዝቦች አንድነት አልተሳካላቸውም ነው ያሉት።
 
መደበኛ ህይወቱን የቀጠለው ህዝቡ ባለፉት አመታት በሴረኞች አጀንዳ ልማቱ የተደናቀፈበት በመሆኑ ፤ ጥሪያቸው ሰሚ ያጣ ሆኗል ሲሉ ገልፀዋል።
 
የኦሮሚያ ክልል እንዳይረጋጋ በማድረግ ሀገር ወደ ትርምስ የማስገባት የፖለቲካ ቁማራቸው ቀጥሏል ያሉት ሀላፊው ፤ ህዝብን ከህዝብ ጋር የማጋጨት አጀንዳዎችን በሚዲያዎቻቸው ጭምር እያስተጋቡ ይገኛሉ ነው ያሉት ።
 
ሆኖም የክልሉ ህዝብ በመደበኛ የክረምት ስራዎቹ ላይ ይገኛል ያሉት ሃላፊው ህዝቡ በማሳው የግብርና ስራውን እየሰራ ነው ብለዋል ።
 
በዚህም እስከ አሁንም ከ327 ሚሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን ሃላፊው አስታውቀዋል ።
 
ለ2013 የትምህርት ዘመን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ያነሱት ሀላፊው ተጨማሪ 30 ሺህ መማሪያ ክፍሎች የመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል ።
 
የቢሮ ሀላፊው በመግለጫቸው ማብቂያ ፤ ህዝቡ አንድነቱን እንዲያጠናክር የጥፋት ሀይሎችን የማጋለጥ ስራውን እንዲያግዝ ጠይቀዋል ፤
 
በሀይለየሱስ መኮንን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.