Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መንግስት በክልሉ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
 
የክልሉ መንግስት ውሳኔውን በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፥ ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ግብረ ሀይል አቋቁመሞ ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
 
የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ስኬታማ ለማድረግም የክልሉ መንግስት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
 
በዚህም መሰረት የሰራተኞች በአንድ ቦታ መቆየት እና የስራ ቦታ መጣበብ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረውን ተጋላጭነት ለመቀነስ የቆየ እና በሀኪም ማስረጃ የተደገፈ የጤና እክል ያላቸው ሰራተኞች፣ ነብሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች እንዲሁንም የጡረታ መውጫ ጊዜያቸው የደረሱ ሰራተኞች እረፍት እንዲወጡ የወሰነ ሲሆን፥ በተጨማሪም የመንግስት ስራ በማይበደል መልኩ የዓመት እረፍታቸውን መውሰድ የሚፈልጉ ሰራተኞችም እንዲወጡ ተፈቅዶላቸዋል።
 
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፀጥታ አካላት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ከክልል እስከ ቀበሌ ያሉ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች አሁን ካጋጠመው ችግር እስኪወጣ ድረስ ስራቸውን በከፍተኛ ኃላፊነት እንዲወጡም አሳስቧል።
 
የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ የክልሉ መንግስት ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችን ቢሰራም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ የግል ተቋማት ማለትም ሆቴሎች፣ የመኝታ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት፣ የተለያዩ የመዝናኛ ቤቶች እንዲሁም አንዳንድ የእምነት ተቋማት ከሚተላለፈው መመሪያ በተቃራኒ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ በጤና ባለሙያዎች ከሚሰጡ ትምህርቶችና ምክሮች እንዲሁም ከመንግስት ውሳኔዎች በተቃራኒ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የህግ የበላይነትን የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።
 
ቫይረሱ በሀገራችን ከተከሰተ በኋላ የተለያዩ በጎ አድራጊዎች የተለያዩ ድጋፎችን ቢያደርጉም ከዚህ በተቃራኒ ግን በአቋራጭ ለመበልፀግ ያሰቡ ነጋዴዎች ህገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርጉ ተስተውላል፤ ይህንን ለመከላከል በተሰራው ስራም ከ1 ሺህ 600 በላይ ተቋማት ላይ እርጃ ተወስዷል ያለው የክልሉ መንግስት፤ ቁጥጥሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም በመግለጫው አረጋግጧል።
 
የክልሉ የፀጥታ ዘርፍም በጤና ባለሙያዎች በሚሰጡ ምክርና ትምህርት መሰረት ራሱን ከቫይርሱ በመጠበቅ በህዝቡ ላይ ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ለመከላከል የሚደረገውን እቅስቃሴ ለመደገፍ ዝግጅት እንዲያደርግም በክልሉ መንግስት ጥሪ ቀርቦለታል።
 
ከምንግዜውም በላይ ያለውን አቅም በሙሉ በመጠቀም በኮሮና ቫይረስ አማካኝነት በህዝቡ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመከላከል እንደሚሰራ ያስታወቀው የክልሉ መንግስት፤ ይህንን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ ስለሚወስድ፤ የህግ አስከባሪዎችም በከፍተኛ ጥንቃቄ ይህንን እንዲያስፈፅሙ አቅጣጫ አስቀምጧል።
 
በሙለታ መንገሻ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.