Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ክልል ከውጭ የሚገዛውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሰራ መሆኑን ገለፀ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት ኢትዮጵያ ከውጭ የምትገዛውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየሰራ መሆኑን ገለፀ፡፡

በዚህም ለስንዴ ግዥ የሚውል ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ዓመታዊ ወጪ ማስቀረት ይቻላል ተብሏል፡፡

ይህን እቅድ ለማሳካት ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልል ከ300 ሺ በላይ ሄክታር መሬት በክላስተር እና በመስኖ እርሻ እየለማ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገልጿል፡፡

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኦሮሚያ የማኅበራዊ ክላስር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በባሌ ዞን ባካሄዱት ጉብኝት በዘርፉ እየተሰራ ያለው ስራ ከውጭ የሚመጣውን የስንዴ ግዥ የማስቀረት እቅድን እያሳካ እንዳለ አመላክተዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የአገር ውስጥ የስንዴ ፍላጎትን ለማሟላት ሲሰራ፣ እንደ ሀገር ራሳችንን በምግብ እህል ከመቻል አልፈን ሌሎች ሀገራትን መመገብ እንደምንችል ማሳየት እንችላለን ብለዋል፡፡

አቶ አዲሱ ይህን ስራ የአርሶ አደሩን ሕይወትና የሀገርን መልካም ገጽታ መቀየር የሚችል፤ የክብር ጉዳይ ነው በማለት ገልፀውታል፡፡

ሀገራችን ለረዥም ጊዜያት የምግብ ዋስትና ማሳካትና ግብርናችን ዘምኖ የአርሶ አደሩንና የሀገርን ምጣኔ ሐብት እምብዛም መቀየር እንዳልቻለች የታወቀ ነው፡፡

ከውጭ ሀገር የሚገዛ ስንዴን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ውሳኔ የተደረሰው የአዳማ ዲክላሬሽን ከታወጀ በኋለ መሆኑን አቶ አዲሱ ተናግረዋል፡፡

የዚህ ዲክላሬሽን አንዱ ዓላማ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ የእርሻ ምርቶችን በጥራት፣ በብዛትና በተደጋጋሚ በማምረት የውጭ ምንዛሬን አገር ውስጥ ማስቀረት ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መልኩ ሀገር ውስጥ የሚቀር የውጭ ምንዛሬ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ ማነቃቃትና የኑሮ ውድነትና መቀነስ ውስጥ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይታመናል፡፡

የኦሮሚያ ክልል እርሻን ለማዘመን የክልሉ መንግሥት በቅርቡ ከ700 በላይ ትራክተሮችን፣ ከ4000 በላይ የውሃ ፓምፖችን፣ ከ80 በላይ ኮምባይነሮችን ለአርሶ አደሩ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

በቅርቡም ወደ 2000 ትራክቶሮችንና በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮምባይነሮችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እየሰራ እንዳለ አቶ አዲሱ ገልጸዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.