Fana: At a Speed of Life!

የክልሉ መንግስት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል – አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ።

የኦሮሚያ ክልል የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በንቅናቄ መድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የክልሉ መንግስት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ባለሃብቶች ዘርፉን ለማጠናከር በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአምራች ኢንዱስትሪውን በማጠናከር ከዘርፉ ሊገኝ የሚገባውን ጥቅም ማግኘት እንደሚገባም በመድረኩ ተጠቁሟል።

” ኦሮሚያ፡ ኢትዮጵያ ታምርት” በሚል መሪ ቃል ንቅናቄው እየተካሄደ ሲሆን ፥ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ የተሳተፉ ባለሃብቶች ተሳትፈውበታል።

በክልሉ ያለው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በተከሰተው የፀጥታ ችግር እና የኮቪድ-19 ተፈትኖ የነበረ ቢሆንም በዚህ ውስጥም አልፎ ዘርፉ እያደገ መምጣቱ ተነግሯል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ በክልሉ እውቅና የተሰጣቸው 20ሺህ ኢንቨስትመንቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ፥ ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ በአምራች ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ናቸው ተብሏል።

በመድረኩ በክልሉ የአምራች ዘርፍ ችግሮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ሲሆን ፥ ለአምራች ዘርፉ ፍቃድ ከተሰጠ በኋላ ወደ ስራ መግባታቸውን መከታተል ላይና ወደ ስራ ከገቡ በኋላምን በታሰበለት ልክ እየሰሩ መሆኑን መከታተል ላይ ክፍተት እንዳለም ተነስቷል።

በተጨማሪም የአምራች ዘርፉ የማህበረሰቡን ኑሮ በማሻሻል ረገድ ሊኖረው የሚገባውን ጥቅም ማስገኘት እንዲችል ሊሰራበት ይገባል ተብሏል።

የንቅናቄዉ ተሳታፊዎች በስራ ሂደት ዉስጥ ያጋጠሟቸዉን ተግዳሮቶች በማንሳት ከክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊዎችና ከመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ዉይይት እንደሚያካሄዱ ይጠበቃል።

በትግስት ብርሃኔ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.