Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የማሰልጠኛ ማእከላት ስልጠና የወሰዱ አባላቱን አስመረቀ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ የማሰልጠኛ ማእከላት የተለያዩ ስልጠናዎችን የተከታተሉ አባላቶቹን እለት አስመረቀ።

ኮሚሽኑ ለስድስት ወራት በሁርሶ፣ አላጌ፣ አዋሽ ቢሾላና በሰንቀሌ ማዕከላት ያሰለጠናቸውን የፖሊስ ልዩ ሃይል አባላቱን ነው በአዋሽ ቢሾላ ወታደራዊ ሙያ ማሰልጠኛ ማእከል በዛሬው እለት ያስመረቀው።

በምረቃው ላይም የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል እና የክልል ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት፥ ህግና ስርዓት መሬት ወርዶ እንዲተገበርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ በስነ ምግባር የታነፀ የፀጥታ ኃይል ድርሻው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

መንግስት የክልሉን ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅና የለውጡ ጉዞ ከዳር ለማድረስ የፀጥታ ኃይሉን በአዲስ መልክ እያደራጀ መሆኑን ተናግረዋል።

የፖሊስ ሰራዊቱ የሚጠበቅበትን ግዴታ እንዲወጣ በየደረጃው የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል ተገቢውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርግለት ጠይቀዋል።

የፖሊስ ልዩ ኃይል አባላት ሙያው የሚጠይቀውን ስነ- ምግባር በመጠቀምና በብቃት በመወጣት ሀገራዊ ለውጡን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የማሸጋገር ተልዕኳቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው፥ በክልሉም ሆነ በሀገር ደረጃ አስተማማኝ ሰላም እንዲመጣና የህግ የበላይነት እንዲከበር የክልሉን ፖሊስ ልዩ ኃይል በአዲስ መልክ ማደራጀት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

“የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ ካልተቻለ ሀገሪቱ ሰላም ልትሆን አትችልም” ያሉት ኮሚሽነሩ ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ በብቃት እንዲወጡ አስገንዝበዋል።

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው ተመራቂዎች፥ በስልጠና ሂደት ያገኙትን በተግባር የተደፈ ስልጠና የሀገርን እና የህዝብን ሰላም ለማስጠበቅ አንደሚጠበቁት ገልፀዋል።

እንዲሁም በክልሉም ብሎም በሀገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲከበር ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.