Fana: At a Speed of Life!

የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ የጠ/ሚ ዐቢይን የጀግንነት ፈለግ በመከተል የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ እንዲደግሙ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን የጀግንነት ፈለግ በመከተልና የሀገር መከላከያን በመቀላቀል ዛሬም እንደትናንቱ የአባቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ እንዲደግሙ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ጥሪ አቀረቡ።

ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባወጡት መግለጫ፥ ዛሬም እንደትናንቱ ሀገሪቱ የተደቀነባትን የህልውና አደጋ ለመመከት እየተደረገ ባለው ሁሉ አቀፍ ተጋድሎ የኦሮሞ ወጣቶች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያስተላለፉትን ሀገር አድን ጥሪ በመቀላቀል የወያኔንና ግብረ አበሮችን ቀብር ለማፋጠን በጀግንነት ወኔ ለሀጋራዊ ክብር መሰዋትነት በመሽቀዳደም ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

የመግለጫቸው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
 
ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የቀረበ ጥሪ
 
መሪውን ያጀገነ ህዝብ የታሪክ ተቋዳሽ ይሆናል !
,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,,
 
በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ወንድም ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመተባበር ባደረገው ተጋድሎ ኢትዮጵያን በደምና አጥንት ጠብቆ ያቆየ ህዝብ መሆኑ የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ በዚህ ሀገረ-መንግስት ግንባታ፤ ሀገራዊ ነጻነትና ሉዓላዊነትን አስጠብቆ ለማስቀጠል በተደረገው ተጋድሎ በርካታ መሪዎችን ያፈራና ያጀገነ፤ በነዚሁ ጀግኖች መስዋዕትነት ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ እንድትኖር ያደረገ ህዝብ ነው፡፡ በሁሉም የትግል አውድ የተፈጠሩ የኦሮሞ ጀግኖች በአሸናፊነታቸው ሀገራቸው ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ መድረክ ስሟ ገኖ እንዲናኝ፤ ሰንደቋ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ፤ ስመ ገናና ኩሩ የጀግኖች ሀገር ሆና እንድትታውቅ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ወታደር ሆነው ጦር በመምራት ወራሪና ከሃዲ ባንዳን የሀፍረት ካባን አከናንበዋል፡፡ በአለም አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ኢትዮጵያን ከፍ አድርገዋታል፡፡ በግብርናውም አርሰው ከማብላት አልፈው ለሀጋራዊ ምጣኔ ሀብት የብረት ምሰሶ የሆኑ በርካታ ጀግና አርሶ አደሮችም ተፈጥረዋል፡፡
 
የኦሮሞ ህዝብ በሚወዳት ሀገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ አደጋ በተጋረጠበት ዘመን ሁሉ መሰዋዕትነት በመክፈል ሀገራዊ ህልውና እንዲቀጥል ለመሰዋዕትነት የሚሽቀዳደሙ ጀግኖችን ያፈራ ህዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያን እልፍ አዕላፍ የጀግንነትና የአልበገሬነት አርማ፤ የጥቁር አፍሪካውያን የነጻነት ተምሳሌት የሆነው የዓድዋ ድል ታሪክ በአለም ድንቅ የታሪክ መዝገብ እንዲመዘገብ በተደረገው ሁሉ አቀፍ ተጋድሎ የኦሮሞ ጀግኖች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይህ በመሆኑም በጥቁሮችና ነጮች መካከል የነበረውን የበታችነትና የበላይነት መስተጋብር ምዕራፍ በመዝጋት የነጻነትና የእኩልነት ጸሃይ በአፍሪካ ምድር እንዲፈነጥቅ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዓድዋ፤ ማይጨው፤ ካራማራና የመሳሰሉት የጀግኖች ውሎ ማስታወሻ ህያው ምስክር ናቸው፡፡
 
ከቅርብ ታሪክ አንጻርም የኦሮሞ ቄሮ እና ቀሬ እስናይፐር ሳይበግረው፤ እስርና እንግልትን ሳይታክት፤ የወንድሙና እህቱ ሞት ይባሱኑ እንደብረት ጠንክሮ በመቆም በከፈለው ከፍተኛ መሰዋትነት ለ 27 አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲዘርፍና ሲያሰቃይ የኖረውን ስግብግብ ጁንታ ከስር መሰረቱ በመንቀል ለኦሮሞ ህዝብና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መረጋገጥ ጉልህ ድርሻ አበርክተዋል፡፡
 
ዛሬም እንደትላንቱ የተደቀነብንን ሀገራዊ የህልውና አደጋ ለመመከት እየተደረገ ባለው ሁሉ አቀፍ ተጋድሎ የኦሮሞ ወጣቶች ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ያስተላለፉትን ሀገር አድን ጥሪ በመቀላቀል የወያኔና ግብረ አበሮችን ቀብር ለማፋጠን በጀግንነት ወኔ ለሀጋራዊ ክብር መስዋዕትነት በመሽቀዳደም ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህም ዛሬም እንደትላንቱ የአባቶቻቸውን የጀግንነት ፈለግ የተከተሉ ጀግና ሆነው የሚያጀግን አዲስ ተውልድ መፈጠሩን ያሳያል፡፡ ሀጋራዊ ነጻነትና ሉዓላዊነትን ማስከበር የሁሉም ትውልድ ግዴታ ነው፡፡
 
ከሁሉም በላይ ይህ ትውልድ ጀግኖ የሚያጀግን መሪ ታድሏል፡፡ ከጀግና መሪ ጎን የቆመ ህዝብ ደግሞ ታሪኩን ያድሳል፡፡ ገናና፤ ነፃና አይበገሬ ህዝብ ሆኖ ይቀጥላል፡፡ መሪውን የበለጠ ያጀግናል፡፡መሪውን ያጀገነ ህዝብ የታሪክ ተቋዳሽ ይሆናል፡፡
 
በመሆኑም የኦሮሞ ቄሮና ቀሬ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የጀግንነት ፈለግ በመከተልና የሀገር መከላከያን በመቀላቀል ዛሬም እንደትናንቱ የአባቶቻችሁን የጀግነነት ታሪክ እንድትደግሙ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ስም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
 
ሽመልስ አብዲሳ
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት
ህዳር 22/2014
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.