Fana: At a Speed of Life!

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የመሬት ፕላን ሥራውን አጠናክሮ እየሠራ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ያላቸውን ወሳኝነት ተገንዝቦ የመሬት ፕላን ሥራውን አጠናክሮ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢዎች ሪፎርም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ካሊድ አብዱራህማን እንደገለጹት ፥ ሚኒስቴሩ የኢትዮጵያን ከተሞች ልማት ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ወሳኝነት ተገንዝቦ የመሬት ፕላን ስራውን አጠናክሮ እየሠራ ነው፡፡

የከተማ መሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ስርዓትን በማዘመን በከተሞች ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ የሚታየውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመቅረፍ የሰው ኃይል ማፍራት ትልቁ ተግባር መሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለቴክኖሎጂ ሽግግር ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ይገዙ ባደረጉት ንግግር ፥ በከተሞች የሚስተዋለውን የመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች የአሠራር ችግር በሰለጠነ ባለሙያ መቅረፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በንድፈ ሀሳብ፣ በላቦራቶሪ እና በመስክ ቅየሳ ላይ ያተኮረው ይህ ስልጠና ለ45 ቀናት ከ200 ለሚበልጡ ባለሙያዎች እንደሚሰጥም ተመላክቷል፡፡

ስልጠናውንና ምዘናውን የሚከታተሉ ባለሙያዎችም÷ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ ክልሎች የተውጣጡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ እንደገለጹት፥ ዩኒቨርሲቲው ለማህበረሰቡ የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረጉ በኩል የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው፡፡

በአበበች ኬሻሞ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.