Fana: At a Speed of Life!

የከተማዋን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት እየተሰራ ነው –ም/ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚያነሱትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከኢዜአ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገዋል።

በእዚህም ምክትል ከንቲባዋ ወደ ኃላፊነት ቦታው ከመጡ በኋላ የሰሯቸውን ሥራዎች፣ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፣ የመሬት ወረራ እና በአዲሱ የክፍለ ከተማ አደረጃጀት እና የካቢኔ ሹም ሽርን የተመለከቱ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች ለማድመጥና የህዝቡን ፍላጎት ለመረዳት የሚያስችሉ ውይይቶችን ከከተማዋ ነዋሪዎች ጋር ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ኮሮናቫይረስ በተከሰተበት ወቅት ወደ ኃላፊነት መምጣታቸው ፈታኝ መሆኑን ገልጸው፤ ባለፉት ሁለት ወራት ቅድሚያ ሊሰጣቸው ለሚገቡ ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት ማከናወናቸውን ገልፀዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የትራንስፖርት፣ የመጠጥ ውሃ እና የመኖሪያ ቤት ችግሮችን ለማቃለል የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን አብራርተዋል።

ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ለ43 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩንና ከዚህ ወስጥ 48 በመቶ ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ምክትል ከንቲባዋ አንስተዋል።

“በከተማዋ ያለውን ስር የሰደደ የትራንስፖርት ችግር ፣ አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣምና አገልግሎቱን ለማሻሻል የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ” ብለዋል።

ለዚህም ለነዋሪዎች የአጭር ጊዜ እፎይታን የሚሰጡ በርካታ አውቶቡሶችን በኪራይ ወደ ስምሪት በማስገባት ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረግ ላይ መሆኑን ነው በማሳያነት የጠቀሱት።

“ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት 3 ሺህ የሚሆኑ ዘመናዊ የከተማ አውቶቡሶች ግዢ፣ መንገዶችን የማሳለጥ ፣ ተጨማሪ የፓርኪንግ ቦታዎች የማዘጋጀት እና አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ የማዘመን ሥራዎችን በፍጥነት ለመተግበር በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው” ብለዋል።

የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት መንግስት ከሚያስገነባቸው ቤቶች በተጨማሪ አቅምና ፍላጎት ያላቸው በመንግስት መሬትና መሰረተ ልማት ቀርቦላቸው ራሳቸው በማህበር ቤት መገንባት የሚችሉበትና ሌሎች አማራጮች መቀመጣቸውንም ምክትል ከንቲባዋ አስረድተዋል።

ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በተመለከተም የተቆፈሩ የውሃ ጉድጓዶች ወደ ተግባር በማስገባት ለውሃ እጥረቱ አፋጣኝ መፍትሄ ለመስጠት በከፍተኛ ቅንጅትና ርብርብ እየተሰራ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

“ችግሩ በዘላቂነት እንዲፈታ የለገዳዲ እና የገርቢ የውሃ ፕሮጀክቶች ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብለዋል።

ምክትል ከንቲባዋ ከመልካም አስተዳደር እና መንግስታዊ አገልግሎትን በቅርበት ከማግኘት አንፃር ይነሱ የነበሩ የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል አዲስ ክፍለ ከተማ መዋቀሩንም ነው የተናገሩት።

ክፍለ ከተማን ለማዋቀር ጥናቱ ከ1996 ዓ.ም ጀምሮ የተጀመረ መሆኑን አስታውሰው፤ “በተለይ ኮልፌ ቀራኒዮን ጨምሮ ቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች ሰፊ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ነበሩ” ብለዋል።

ክፍለ ከተማው ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ፣ አገልግሎትን ወደ ህዝቡ ለማቅረብ እና የመሬት ወረራና መሬትን በአግባቡ ማስተዳደር እንዲቻል ታስቦ የተዋቀረ  መሆኑን አስረድተዋል።

አዲሱ ክፍለ ከተማ “ለሚ ኩራ” የሚል ስያሜውን ያገኘው ከየካ “ኩራ” ተብሎ የሚጠራን አካባቢ፣ ከቦሌ ደግሞ “ለሚ” የተባለውን አካባቢ በመውሰድና ነዋሪዎች ተወያይተውበት የተወሰነ ውሳኔ መሆኑን በዝርዝር አብራርተዋል።

የክፍለ ከተማ መዋቅሩም አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ሁልጊዜም አገልግሎትን  ለተገልጋዮች በጥራት፣ በፍትሀዊነትና ያለእጅ መንሻ መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የከተማው ካቢኔ የአመራር ሹም ሽርንም በተመለከተ ሙያና ብቃትን ማዕከል ከማድረግ ባለፈ የሴቶችና የከተማዋ ነዋሪዎችን ተሳትፎ ትኩረት ባደረገ መልኩ የአመራር ምደባ መደረጉን ገልፀዋል።

ከፍተኛ የህዝብ ቅሬታ በሚነሳባቸው አንዳንድ ተቋማት የአመራር ምደባ እንደገና መሰራቱን የገለፁት ምክትል ከንቲባዋ፤ በዚህም የሴቶች ተሳትፎ ከ20 በመቶ ወደ 35 በመቶ ከፍ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ከፍተኛ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጥያቄ እንዳለው አስታውሰው፤ ይሄንን ችግር ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ነድፎ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ከመሬት ወረራ ጋር አያይዘው በሰጡት አስተያየትም በዚህ ህገ ወጥ ተግባር የመንግስት ሥራ ኃላፊዎች፣ ሠራተኞችና ደላሎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገልፀዋል።

በሪፎርም ሥራው ይሄንን ችግር ለመፍታት ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት የመሬት ባለቤትነት ህጋዊነትን የሚያጣራ ግብር ኃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በቴክኖሎጂ የተደገፉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጭምር  ነው የተናገሩት።

ህብረተሰቡ በከተማዋ የተጀመሩ ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ወይዘሮ አዳነች ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.