Fana: At a Speed of Life!

የከተራና የጥምቀት በዓላት የኮቪድ-19 መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ይከበራሉ – ቤተክርስቲያኗ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕዝበ ምዕመኑ የከተራና የጥምቀት በዓላትን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር እንዲያከብር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አሳሰበች።

የከተራና የጥምቀት በዓላት በመላው ኢትዮጵያ የክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥር 10 እና 11 ቀን ይከበራሉ።

የዕምነቱ ተከታዮች በዓሉን ከዋዜማው ከተራ ጀምሮ በተለያዩ ኃይማኖታዊና ባሕላዊ ስነ-ስርዓቶች ያከብሩታል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ የከተራና የጥምቀት በዓላትን ለማክበር እየተደረገ ስላለው ዝግጅትና ኮቪድ-19ን ለመከላከል መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ ለኢዜአ ገልጸዋል።

ዘንድሮ በዓላቱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር መወሰድ ያለባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ በማድረግና ለሰዎች ጤና በመጠንቀቅ የሚከበር ነው ብለዋል።

ገዳማትና አድባራትም የከተራና የጥምቀት በዓላት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበሩ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በዓሉ ሠላማዊ ሆኖ እንዲከበር ቤተክርስቲያኗ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን ጨምሮ ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋራ በመሆን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓንም ብፁዕነታቸው አስታውቀዋል።

ሕዝበ ምዕመኑ በዓሉን ሲያከብር የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድና ለበዓሉ ሠላማዊ ሆኖ መከበር የበኩሉን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አሳስበዋል።

ከተራና በጥምቀት በዓላት ዲፕሎማቶች፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ቱሪስቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።

ብፁዕ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓሉ የሠላም፣ የጤና የደስታ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት /ዩኔስኮ/ ታሕሳስ 2012 ዓ.ም የጥምቀትን በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስነት መዝግቦታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.