Fana: At a Speed of Life!

የከፍተኛ ትምህርት ጥራት አግባብነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሙያ ማህበራት ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)የከፍተኛ ትምህርት ጥራት አግባብነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የሙያ ማህበራት ከመንግስት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ተጠይቋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ከከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ በመሆን የሙያ ማህበራት ሚና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚል መርህ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በዉይይት መድረኩ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ አመራሮች፣ የተለያዩ የሙያ ማህበራት ሀላፊዎችና ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት አካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀኔራል ዶክተር ኤባ ሚጅና÷ የትምህርት ጥራት አግባብነት እና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሙያ ማህበራት የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ተሳትፏቸዉ እንዲጠናከር የበኩላችን ድርሻ መወጣት አለብን ብለዋል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ ፤ መድረኩ በቀጣይ ስራዎች የሙያ ማህበራት በከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ላይ ያላቸዉን ተሳትፎ በማጠናከር ለዉጤቱ መሳካት የድርሻቸዉን እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነዉ ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታዉ ባለፉት 10 አመታትም የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ የተሰሩ ስራዎች በርካታ መሆናቸዉን ገልጸዉ ÷ ይህንን በማሳካት ረገድ የሙያ ማህበራት በስርዓተ ትምህርቱ ቀረጻ፣ ክለሳና ግምገማ ድርሻቸዉ የላቀ በመሆኑ በቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከማህበራቱ ጋር ያለዉን ግንኙነት በማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር አንዷለም አድማሴ በበኩላቸዉ ÷ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነትን በማረጋገጥ በኩል እየሰሯቸዉ ያሉ ስራዎችንና እየገጠሟቸዉ ያሉ ተግዳሮቶችን በመጥቀስ የሙያ ማህበራት በየሙያ መስካቸዉ ክትትል በማድረግ ከመንግስት ጋር በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሲቪል ማህበራት ማስተባበሪያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጃማ ደጋጎ በበኩላቸዉ÷ ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሙያ ማህበራት ጋር መስራቱ ለማህበራቱ በቂና ብቁ አባላትን ለማፍራት ጠቀሜታ ያለዉ ነው ብለዋል።

አያይዘውም አገራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከሙያ ማህበራት ጋር ተባብሮ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

የሙያ ማህበራቱም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በጋራ የሚሰሩ መሆኑን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡-
https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.