Fana: At a Speed of Life!

የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመሆናችን ምስክር ነው- መንግስት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመሆናችን ምስክር ነው አለ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ዛሬ እየታሰበ ያለውን የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን ምክንያት በማድረግ መግለጫ አውጥቷል።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የካቲት 12 እኛ ኢትዮጵያዊያን በጠላት ስንነካና ስንጠቃ ይበልጥ የምንጠናከርና የምንሰባሰብ ስለመሆናችን ምስክር ነዉ!
የካቲት 12 በኢትዮጵያ ታሪክ ልዩ ስፍራ ያለዉ ዕለት ነዉ፡፡ ዕለቱ የዛሬ 92 ዓመት ገደማ በኢትዮጵያዊያን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ የተፈፀመበት ቀን ነዉ፡፡ ለዘመናት የኢትዮጵያ ጠላቶች ኢትዮጵያዊያንን በኃይል በማንበርከክ ምኞታቸዉን እውን ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል፡፡
ሙከራዎቻቸዉም ሳይሳካ ሽንፈት ተከናንበዉ ተመልሰዋል፡፡
በ1888 ዓ/ም ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለመያዝ የጣሊያን ጦር ዘመናዊ መሳሪያን ታጥቀዉ መጣ፡፡ ሆኖም ግን ባልተለመደ ሁኔታ እስከ አፍንጫዉ የታጠቀዉ ዘመናዊና ግዙፉ የአዉሮፓዊት አገር የጣሊያን ጦር ብርቱ ልብ እንጂ ይኼ ነዉ የሚባል ዘመናዊ መሳሪያ ባልነበራቸው በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች ተሸነፈ፡፡ ይህ ሽንፈት ለኢትዮጵያ ጊዜ የማይሽረዉ ታሪካዊ ድል ቢሆንም ወራሪዉን ኃይል አንገት ያስደፋ የዉርደትና ቅሌት ጦርነት ነበር፡፡ ከዚህ አስከፊ ዉርደት ለማገገምና ኢትዮጵያን ለመበቀል በወቅቱ የጣሊያን ገዥ ቢኒቶ ሙሶሎኒ ከ40 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን ወረራት፤ ለጊዜዉም ቢሆን የጦር የበላይነት አግኝቶ የተወሰኑ ከተሞችን ያዘ፡፡ ሆኖም ግን ለነፃነታቸዉ የማይተኙና ባርነትን የማይቀበሉ የኢትዮጵያ ልጆች ለወራሪዉ ኃይል የእግር እሳት ሆኑባቸዉ፡፡ በተለይም በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ/ም በአዲስ አበባ ስብሰባ ሲመራ በነበረዉ የፋሺሽቱ እንደራሴ የነበረዉ ማርሻል ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ በነፃነት ታጋዮች የግድያ ሙከራ ተደረገበት፡፡
ሙከራዉን ተከትሎ ድርጊቱ ያበሳጨዉ የፋሺሽቱ ጦር ለሦስት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ፈፀመ፡፡ ከ20,000 – 30,000 የሚገመቱ ንፁሃን ዜጎች ጭካኔ በተሞላበት አኳኋን በጅምላ ተጨፈጨፉ፡፡ ዕለቱም እስከ ዛሬ ድረስ የየካቲት 12 ሰማዕታት መታሰቢያ ሆኖ ይዉላል፡፡
ምንም እንኳን የጠላት ምኞት ኢትዮጵያዊያን ዳግም ለነፃነታቸዉ እንዳይታገሉ ለማስተማር የተደረገ ቅጣት ቢሆንም እርምጃዉ ጀግኖቹን ይበልጥ አጠናከራቸዉ እንጂ ከነፃነት ትግላቸዉ ፈፅሞ ሊያስቆማቸዉ አልቻለም፡፡ እንዲያዉም ኢትዮጵያዊያን በጠላት ሲጠቁ እጅ የሚሰጡ ሳይሆኑ ይበልጥ የሚጠነክሩና እንደ ንብ አንድ የሚሆኑ፣ ለጠላት የማይመቹ ህዝቦች መሆናቸዉን አረጋገጡ፡፡ ጭፍጨፋዉ ይበልጥ ጀግኖች አርበኞች ተደራጅተዉ ጠላትን እንዲያርበደብዱ ጉልበት ፈጠረላቸዉ እንጂ ተስፋ አላስቆረጣቸዉም፡፡ ጠላትን እንቅልፍ ነሱ፣ ብሎም ከነአካቴዉ ከአገራችን አባረሯቸዉ፡፡
ይህ ለጠላት የማንመችና የማንንበረከክ፣ ነፃነት ወዳድ መሆናችን ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ጠላት ምኑንም ያህል ቢደረጅ፣ ቢዶልት፣ ቢያሴርና ቢተባበር የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዉያን ይበልጥ አንድ የመሆንና ችግርን የመቋቋም እሴት ዛሬም አገራችንን ከብተና አድኗል፤ ለጠላት ያለመንበርከክና አሸናፊነት የጋራ ታሪካችን ብቻም ሳይሆን የጋራ ባህላችን ሆኖ ለትዉልድ ተርፏል፡፡ ይህ የኢትዮጵያዊያን የጋራ እሴት ላልገባዉ ጠላት የጥንካሬአችን ምንጭ ትንግርት ሆኖበታል፡፡
ዘንድሮ የየካቲት 12 ሰማዕታትን ስንዘክር የጥንካሬአችን ምንጭ የሆነዉን የመተባበር ባህላችንን በማጠናከር፣ አንድነታችንን ጠብቀን ዘርፈ ብዙ ጠላቶቻችንን በማሸነፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በመትጋት ሊሆን ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ በብዙ ዜጎቿ መሥዋዕትነት የጸናች ብርቱ ሀገር ለመሆኗ የየካቲት 12 ሰማዕታት ህያው ምስክሮች ናቸው።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.