Fana: At a Speed of Life!

የክላስተር እርሻ ተሞክሮን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን የተመራ ልዑክ በክልሉ አብርሃሞ ወረዳ የመኸር እርሻ እንቅስቃሴን ጎብኝቷል፡፡

በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳድሩ በአብርሃሞ ወረዳ የተጀመረው የክላስተር እርሻ የሚበረታታ መልካም ጅምር መሆኑን ገልፀው ይህን ጅምር በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ማስፋፋት ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ አሻድሊ አክለውም እንደ ክልል በዚህ የመኸር እርሻ ሁሉም መታረስ የሚችል መሬት በዘር መሸፈን አለበት ተብሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚቻለው በዚህ መንገድ በመሆኑ አርሶ አደሩ በዚህ ልክ ወደ ስራ መግባት አለበትም ነው ያሉት፡፡

የግብርና ባለሙያ ስራው ቢሮ ውስጥ አይደለም ያሉት አቶ አሻድሊ ሁሉም የግብርና ባለሙያ ወደ ታች ወርዶ አርሶ አደሩን በቅርበት ሊደግፍ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበክር ሀሊፋ በበኩላቸው፥ በዘንድሮው አመት የግብርናውን ስራ የሚደግፉ 24 ትራክተሮች መሰራጨታቸውን እና የግብአት አቅርቦት የተገኘውን ማሰራጨት ቢቻልም አቅርቦቱ በቂ ባለመሆኑ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያን እንዲጠቀም ለማስቻል መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

የአብርሃሞ ወረዳ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አታላይ ደረጀ፥ በዚህ አመት ከ93 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመኸር እርሻ ለማረስ ታቅዶ እስካሁን ከ79 ሺህ 853 ሄክታር በላይ መታረሱን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥ 23 ሺህ 250 ሄክታር በላዩ መሬት በኩታ ገጠም የታረሰ መሆኑን መግለፃቸውን ከክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.