Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች ለ1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አድሀ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የክልል ርእሳነ መስተዳድሮች 1 ሺህ 441ኛው የኢድ አል አደሀ (አረፋ) በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ በመልእክታቸውም የህዝባችን የአንድነትና የአብሮነት በዓላት ከሆኑት ኢድ አልአደሃ አረፋ አንዱ እና የምንኮራበት ነው ብለዋል።

በዓሉ ከእስልምና እምነት ተከታዮች አልፎም በመተጋገዝና በመደጋገፍ እሴቱ የሚታወቅ ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፥ የተቸገረውን መርዳት፣ የተራበውን ማብላትና የታረዘውን ማልበት የህንቱ ተከታዮች ተግባራት በመሆኑም ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።

የኦሮና ቫይረስ በዓለም ላይ የኢኮኖሚ ችግር የከፋ እንዲሆን ባደረገበት በዚህ ወቅት የመተጋገዝና የመተባበር እሴቶች ትልቅ አስተዋዕኦ እያበረከተ ነው፤ ይህም መጠናከር እንዳለበት አስታውቀዋል።

የኢድ አል አድሃ/ አረፋ በዓል ሲከበርም  ራሳችንንና ህዝቡን ከኮሮና ቫይረስ በመከላከል መሆን እንደሚገባውም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአማራ ክልል ረእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእከት፥ “የዘንድሮው የኢድ አል አደሀ በዓል በምናከብርበት ወቅት በአንድ በኩል የገጠሙንን ውስብስብ ችግሮች በጋራ ተሻግረን በክልላችን አንፃራዊ ሰላም እና መረጋጋት የሰፈነበት፤ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት የጀመረበት እና አንድነታችን የተጠናከረበት እንዲሁም የታላቁ የህዳሴ ግድባችን የመጀመሪያውን ዙር የውሃ ሙሌት በማሳካት የግድቡን እውን መሆን ትልቅ ተስፋ ያገኘንበት ወቅት ነው” ብለዋል።

“ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ ላመጣነው አበረታች ለውጥ ትልቅ እገዛ እንዳደረገ ሁሉ ያሉብንን ስጋቶችንም በቁርጠኝነት ለመከላከል ሁሌም ከጎናችን እንደሚቆም ያለኝ እምነት የፀና ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

የኢድ አል አረፋ በዓል ማእድ በማካፈል የሚከበር በዓል  በመሆኑን የገለፁት አቶ ተመስገን፥ “በዓሉን ስታከበሩ በሀገራችን ድጋፍ የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን በማስታወስ እና በመደገፍ እንደሚሆን አምናለሁ” ብለዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የኢድ አል አደሀ (አረፋ) በዓልን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፥  አረፋ ሰዎች ይበልጥ የሚደጋገፉበት እና የሚተሳሰቡበት ታላቅ በዓል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው አክለው እንደጠቆሙት የዘንድሮውን የአረፋ በዓል በተለመደው መንገድ እንዳናከብር የኮሮና ቫይረስ ባስከተለው ጫና ምክንያት አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ግድ እንዲል ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

እናም የበዓሉ ዋና አላማም መደጋገፍና መተሳሰብ እንደመሆኑ መጠን ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር እንደ ከዚህ ቀደሙ በጋራ አብሮ በመብላትና በመጠጣት ሳይሆን አካላዊ ርቀቱን ጠብቆ በያለበት ሆኖ እንዲያከብርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም፥ “ለመላው ሙስሊም እህቶቼና ወንድሞቼ እንኳን ለኢድ አል አድሀ/አረፋ በዓል በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለው” ብለዋል።

በዓሉ ሲከበር እንደቀደመው ጊዜ መሰባሰብ በጋራ ማክበር ላይኖር ይችላል፤ ሆኖም ይህ ጊዜ አልፎ በዓሉን በጋራ የምናከብርበት፣በፍቅር የምንሰባሰብበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን እምነቴ የፀና ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በዓሉ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህላችሁን ከፍ አድርጋችሁ የምታሳዩበት፤ ወገናችሁን የምታስቡበት እንደሚሆን አምናለው፤ ከአጥራችሁ ባሻገር የጎደለባቸውን አሉና እነሱን በመደገፍ እንድታከብሩም አደራ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድም እስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ 1441ኛው የዒድ አል -አድሃ (አረፋ) በአል በሰላም አደራሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ 1441ኛውን የዒድ አል -አድሃ (አረፋ) በአልን ሲያከበር ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ማክበር እንዳለበት ም አሳስበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን በአልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት እርስ በእርስ በመደጋገፍና ማዕድ በመጋራት በአብሮነት በአሉን ማክበር እንዳለበትም ገልፀዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንም በመልእክታቸው፥ ህዝበ ሙስሊሙ 1441ኛውን የዒድ አል -አድሃ (አረፋ) በአልን ሲያከበር ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።

የዘንድሮውን የኢድ- አል አድሃ (አረፋ) በአል ስናከበር ታላላቅ ስኬቶችና ተግዳሮቶች እንደነበሩ በመግለጽ ከስኬቶቹ ውስጥም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መያዙ አንዱና ዋነኛው ነው ብለዋል ፡፡

የኢድ አል አድሃ በአልን ስናከበር ራሳችንና ቤተሰቦቻችንን ከኮሮና ቫይረስ እየተከላከልንና መንግስት ካወጣው ከአስቸካይ ጊዜ አዋጅና የጤና ሚኒስቴር ባስቀመጣቸው የጤና መመሪያዎችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝበ ሙስሊሙ በአሉን ማክበር እንዳለበትም ገልጸዋል፡፡

ከኢድ ሶላትና በአሉን ተንተርሶ በሚከናወኑ የግብይት ስርአቶች ጋር ተያይዞ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ የበአሉ ስነ ሰርአት መፈጸም እንዳለበትም አሳስበዋል።

የሐረሪ ክልለ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪም የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ ህዝበ በዓሉን ሲያከበር ራሱን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ማክበር እንዳለበት ጥር አቅርበዋል።

ህዝበ ሙስሊሙ የኢድ አል አድሃ አረፋ በአልን ሲያከብር የተቸገሩትን በመርዳት እርስ በእርስ በመደጋገፍና በአብሮነት በአሉን ማክበር እንደሚገባ ገልፀዋል።

ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮችም በአሉ የሰላም፤ የአንድነትና የጋራ በአል እንዲሆን ርእሳነ መስተዳድሮቹ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.