Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እና ከንቲባዎች የዒድ አልፈጥር በዓል መልካም ምኞት መልዕክት እያስተላለፉ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 15፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች እና ከንቲባዎች የ1441ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል መልካም ምኞት መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል ርእስ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመልካም ምኞት መልዕክታቸው የሙስሊሙ ማህበረሰብ ልዩ እና የተቀደሰ የረመዳን ወር ማሳለፉን በመግለፅ ለዘንድሮው የዒድ አልፈጥር በዓል እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን አብሮ አደረሰን ብለዋል።

ዓለም ብሎም ሀገሪቱ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ፈተና ውስጥ በገባችበት ወቅት ላይ ያረፈው የረመዳን ወቅት በመረዳዳት እና በመደጋገፍ ማለፉን ያመለከቱት አቶ ሽመልስ፥ በዚህ በዓል ወቅትም ይህ እንዲደገም ነው ያሳሰቡት።

የደቡብ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በበኩላቸው ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው የኢድ አልፈጥር በዓል በአደባባይ ወጥተን በድምቀት የምናከብረው ቢሆንም ዘንድሮ በዚህ መልኩ ለማክበር የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩን ነው ያመለከቱት።

በመሆኑም ህዝበ ሙስሊሙ ለበዓሉ በሚያደረገው ዝግጅት ሁሉ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለ1441ኛው የዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው “ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም እና በጤና አደረሳቹህ” ብለዋል።

ይህ በዓል ምስጋና፣ ፍቅር፣ ደስታ እና ይቅርታ የተሞላበት ይሁንላችሁ ያሉት ወይዘሮ አዳነች፥ በዓሉን ስናከብር አቅም የሌላቸው ወገኖችን ባለመርሳት የደስታችሁ ተካፋይ እናድርጋቸው አክብሩ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

“ደስታ እና በዓል የማያውቀውን የኮሮና ወረርሽኝ ባለመርሳት ለእራሳችን እና ለቤተሰቦቻችን ከፍተኛውን ጥንቃቄ ማድረግ እና ህጎቹን ማክበር እንዳንዘነጋ” በማለት አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማም ባስተላለፉት መልዕክት “ታላቁን ወር ከልብ በሆነ ፆምና ስግደት አሳልፏችኋል፣ ለራስና ለቤተሰባችሁ እንዲሁም ለሀገራችሁ በመፀለይ ከራሳችሁ አልፋችሁ ለህዝባችሁ ጤና ለምናችኋል፤ የተቸገሩ ጎረቤቶቻችሁን በመርዳት የተቀደሰውን ወር በመልካም ተግባር አሳልፋችሁታል፤ እነሆ ታላቁ የፆም ወቅት አልፎ ለዚች ቀን ስለበቃችሁ እንኳን አደረሳችሁ” ብለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.