Fana: At a Speed of Life!

የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለብርሃነ ጥምቀቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 10፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ለብርሃነ ጥምቀቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ለብርሃነ ጥምቀቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በመልዕክታቸው፥ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ሰዎችን በፍቅር እርስ በእርስ የሚያስተሳስር በርካታ እሴቶችን የያዘ ነው ብለዋል።
“ሰው ከፈጣሪው ይቅርታ እና ምህረትን ለማግኘት ለወዳጆቹ እና ለሰው ልጅ በሙሉ ይቅርታን ማድረግ አለበት” ያሉት አቶ ሽመልስ፥ “እንደ ሀይማኖት አስተምህሮ ደግሞ ሰው ከፈጣሪው ይቅርታ ለማግኘት የተቸገረን መርዳት፣ የተራበ እና የተጠማን በማብላትና በማጠጣት ይረጋገጣልም” ነው ያሉት።
“ሀይማኖታዊ አስተምህሮው ቅንነትን ማብዛት መልካም መሆኑን ያስተምራል” ያሉ ሲሆን፥ ይህ ደግሞ ፍቅርን ለማብዛት፣ ወንድማማችነትን ለማሳደግ እና እርስ በእርስ መተዛዘንን የሚያጠናክር በመሆኑ፤ በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥም ትልቅ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግልም ነው የተናገሩት።
“የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ስናከብር እርስ በእርስ ከመተጋገዝ እና ከመረዳዳት ጎን ለጎን፤ ራሳችንን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ በጠበቀ መልኩ ለሆን ይገባል” ሲሉም አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡም ለኮቪድ መከላከያ የሚሆኑ ቁሳቁሶችን እርስ በእርስ ስጦታ በመሰጣጠት እና በመካፈል በዓሉን በሰላም እና በጤና እንዲያከብርም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር የጥምቀትን በዓል በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

“የዘንድሮው የጥምቀት በዓል ትልልቅ ድሎችን ባስመዘገብንበት እና ከፊት ለፊታችን የተጋረጡ ከባድ ፈተናወችን እየተጋፈጥን የምናከብረው በዓል በመሆኑ ከዚህ ቀደም ካከበርናቸው በዓላት ለየት ይላል” ብለዋል።

ወቅቱ ትላልቆቹን የጥፋት መሀንዲሶች በተባበረ ክንድ ድል የነሳንበት ቢሆንም የዘሩት የጥላቻ ዘር በአንዴድ ጊዜ ተነቅሎ የሚጠፋ ባለመሆኑ አሁንም ከውስጥም ከውጭም የተቀናጁ የጥፋት ሙከራወች እና ከባባድ ፈተናወች መኖራቸውንም አንስተዋል።

የጥምቀት በዓል ከሀይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ የክልሉን ገፅታ የበለጠ የሚገነባበትና በመሆኑም እንግዶችን በፍቅር ተቀብሎ በማስተናገድ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳም ለክርስትና እምነት ተከታዮች የጥምቀትን በዓል ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በመልእክታቸው፥ ህብረተሰቡ በዓሉን ሲያከብር እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የመረዳዳት እና የመደጋገፍ ባህሉን በማጠናከር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
“ዘንድሮ ያጋጠመን የኮቪድ 19 ፈተና ደግሞ ሰብሰብ ብለን በአደባባይ በምናከብራቸው በዓላት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፉ አይቀርም” ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በዓሉን ስናከብር የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በማድረግ በተቻለ መጠን አካላዊ ርቀታችንን በመጠበቅ ሊሆን ይገባል” ብለዋል።
በዓሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የሰላም የጤና የአብሮነትና የብልጽግና በዓል እንዲሆን መልካም ምኞታቸውንም ገልፀዋል።
የሐረሪ ክልል መስተዳድርም በክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ጥር 10 እና 11 ቀን የሚከበሩት የከተራ እና የጥምቀት በዓላት ከሃይማኖታዊ በዓልነት ባሻገር የሀገሪቱ መልካም ገጽታን በመገንባት እና የቱሪስት ፍሰትን ከማጎልበት አንጻር ጉልህ ሚና እንዳላቸው ገልጿል።
በዓሉ ሲከበር የክልሉን ሰላም፣ አብሮነት፣ አንድነት እና ልማትን በማጎልበት ሊሆን ይገባልም ብሏል የክልሉ መንግስት ባስተላለፈው መልእክት።
የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አሕመድ መሐመድ ቡህም ለብርሃነ ጥምቀቱ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክትን አስተላልፈዋል።
የብርሃነ ጥምቀቱ በዓል መልካም የሆነውን ሁሉ የምንፈጽምበት የሰላም እና የፍቅር፣ የደስታ እና የበረከት እንዲሆን በመመኘት እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።

 

እንዲሁም የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ርእሰ  መስተዳድሩ በመልዕክታቸው በክልሉ  የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የሕዝብ መጨናነቅን በመቀነስ እና ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጥንቃቄ በማድረግ በዓሉን እንዲያከብሩም ጠይቀዋል።

ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.