Fana: At a Speed of Life!

የክልሎችን የእርስ በእርስ ግንኙነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሎች መካከል ያለውን የእርስ በእርስ ግንኙነት በማጠናከር ለሰላም፣ ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የአጎራባች ክልሎች የጋራ ፎረም አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
የኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ የደቡብ ምዕራብ ህዝቦችና የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች ክልል አጎራባች መንግስታት ግንኙነት ፎረም ለመመስረት የሚያስችል መድረክ በሃዋሳ አካሂደዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ዛሕራ ሁመድ እንዳሉት÷ ምክር ቤቱ በህዝቦች መካከል በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ክልሎች በመካከላቸው ችግሮቻቸውን፣የልማት ሥራዎችንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በጋራ የሚያካሂዱባቸው የአጎራባች ክልሎች የጋራ መድረክ ለማቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ አለመግባባቶችን ለማስወገድ የሚረዱ ዘመናዊና ባህላዊ የግጭት መከላከያና ማስወገጃ ስልቶችን በማጥናት፣ የአሰራር ስርዓትና ስልት በመዘርጋት ተቋማዊ አደረጃጀት ለመፍጠር እየሰራ ነው ብለዋል።
አራቱ ተጎራባች ክልሎች በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር ያላቸው መሆኑን የጠቆሙት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ ይህ በጋራ የመኖር እሴት እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የብልጽግና ጉዞ ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የአጎራባች ክልሎች የጋራ ፎረም አስተዋጽኦው የላቀ ነው ብለዋል።
ፎረሙ የልማት፣ የሰላም የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በትኩረት ለማከናወን ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑንም አቶ ደስታ ገልጸዋል።
በመድረኩ የአራቱ ክልሎች የጋራ ፎረም ለመመስረት ዝግጅት የሚያደርጉ ከአራቱ ክልሎች አንድ አንድ ተወካዮችና ከፌዴሬሽን ምክር ቤት የመንግሥታት ግንኙነት የዴሞክራሲያዊ አንድነትና ንቃተ ህገ መንግሥት ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ አባል የሆኑበት ኮሚቴ ተቋቁሟል።
በሲዳማ ክልል አስተናጋጅነት የሚካሄደው የመጀመሪያውን የክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች የጋራ መድረክ የጋራ ኮሚቴው ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ እንደሚያካሂድ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.