Fana: At a Speed of Life!

የኮሮናቫይረስን ለመግታት ሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብ ብቻ ሳይሆን መለየትና መመርመር ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል- ዶ/ር ቴድሮስ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ሰዎችን እንቅስቃሴ መገደብ ብቻ ሳይሆን መለየትና መመርመር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም አስታወቁ።

ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ባስተላለፉት መልእክት፥ የተየለያዩ የዓለም ሀገራት የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ስርጭትን ለመግታት ዜጎቻቸው ከቤት እንዳይወጡ የማድረግ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን ገልፀዋል።

ሆኖም ግን ሀገራት በየግላቸው እየወሰዱት ያለው የዜጎችን እንቅስቃሴ የመገደብ ውሳኔ ብቻውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመዛመት ፍጥነትን ለመግታት በቂ አይደለም ብለዋል።

ሀገራቱ ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ኮሮና ቫይረስን ማጥቃት አለባቸው ያሉት ዶክተር ቴድሮስ፥ ይህንን ለማድረግም ሁለተኛ እድል እንደተፈጠረላቸውም ገልፀዋል።

አሁንም ቢሆን ማፈላለግ፣ መለየት፣ መመርመር፣ ማከም እና መከታተል ላይ ሀገራት ቁርጠኛ ውሳኔ አሳልፈው መስራት ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን፥ ይህም ኮሮናን ለመዋጋት ፈጣን እና ተመራጭ መንገድ ነው ሲሉም ገልፀዋል።

በተለይም ማፈላለግ፣ መለየት፣ መመርመር፣ ማከም እና መከታተል ደካማ የሆነ የጤና ስርዓት ላላቸው ሀገራት የተሻለ እና ተስማሚ አማራጭ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ዶክተር ቴድሮስ አክለውም፥ ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑ ሀገራት ያሳስቡናል፤ ሁሉም ሀገራት በእድሜ የገፉትን ጨምሮ ተጋላጭ የሆነ ህዝብ አላቸው ብለዋል።

ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ የሆኑትን ለመጠበቅና ፍላጎታቸውን ለማሟላት በጋራ መስራት ያስፈልጋል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.