Fana: At a Speed of Life!

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ ግማሽ ቢሊየን ሰዎችን ድህነት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለም ዙሪያ የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ቀውስ ግማሽ ቢሊየን ሰዎችን ድህነት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ተገለፀ።
የዓለማችን ከግማሽ ቢለየን ሰዎች ወደ ድህነት ሊገቡ ይችላሉ የሚለው ማስጠንቀቂያ የወጣው ከተባበሩት መንግስታ ድርጅት ሲሆን፥ ወረርሽኙ በፋይናንስ እና በሰው ልጅ ላይ የሚያስከትለውን ኪሳራ ለመለየት በተሰራውን የጥናት ውጤት መሰረት አድርጎ ሪፖርቱ መውጣቱን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።
 
የጥናቱ ባለቤት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲሆን፥ ጥናቱም በለንደን ኪንግ ኮሌጅ እና በአውስትራሊያ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ባለሙያዎች ነው የተካሄደው።
 
የአውስትራሊያ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ክርስቶፈር ሆይ እንደተናገሩት፥ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ የሚያስከትለው የኢኮኖሚ ቀውስ ከጤና ቀውሱ በእጅጉ የከፋ ነው።
 
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ400 እስከ 600 ሚሊየን ሰዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሳቢያ በሚከሰት የኢኮኖሚ ቀውስ ድህነት ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ የጥናቱ ውጤት ያመለክታል።
 
በጥናቱ ውጤት መሰረትም የዓለማችን የድህነት መጠን በዚህ ደረጃ ሲጨምር ከ30 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን እንደሚችልም ነው የተገለፀው።
 
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሲያበቃም ከ7 ነጥብ 8 ቢሊየን አጠቃላይ የዓለም ህዝብ ውስጥ ግማሽ ያክሉ ድህነት ውስጥ የሚኖር እንደሚሆንም በጥናቱ ተቀምጧል።
 
ከእነዚህም 40 በመቶ ያክሉ በምስራቅ እሲያ እና ፓስፊክ የሚገኙ ሲሆን፥ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ህዝብ ደግሞ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት እና በደቡብ እሲያ የሚገኙ ናቸው ተብሏል።
 
የጥናቱ ውጤትም በቀጣይ ሳምንት የዓለም ባንክ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) እና የቡድን 20 ሀገራት የፋይናንስ ሚኒስትሮች በቀጣይ ሳምንት የሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንደሚቀርብም ታውቋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.