Fana: At a Speed of Life!

ኮቪድ -19 ለመከላከል ይረዳል የተባለው ሀገር አቀፍ የምርመራ መርሃ ግብር ስኬት የህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰረታዊ ነው ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኮቪድ-19 ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይረዳል የተባለው ሀገር አቀፍ የምርመራ መርሃ ግብር ስኬት የህብረተሰቡ ተሳትፎ መሰረታዊ መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ገለጹ።
 
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ÷ የወረርሽኙን መስፋፋትና መሰራጨት በመገንዘብ ህብረተሰቡ በትኩረት የመከላከሉን ተግባር ሊፈጽም ይገባል ብለዋል።
 
ሀገር አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝ ምርመራ እና የመከላከል ተግባራትን የመፈጸም ንቅናቄ የተጀመረ ሲሆን÷ በዘመቻውም 17 ሚሊየን የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ምርመራ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
 
ይህንንም ለማከናወን 200 ሺህ የላብራቶሪ ምርመራዎች እንደሚደረጉ ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
 
ኮቪድ 19 ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የሚረዳ ሀገር አቀፍ የምርመራ እና የመከላከል ተግባር ንቅናቄ ዓላማው የኮሮናን ስርጭት ለመግታት ነው ያሉት ዶክተር ሊያ ÷ ህብረተሰቡ የዘመቻው ዋና ተዋናይ በመሆን እራሱን ቤተሰቡን እና አካባቢውን ከበሽታው የመጠበቅ ድርሻውን ሊወጣና የበሽታው ስርጭት መንስኤ ላለመሆን መጠንቀቅ ይገባል ብለዋል።
 
በዘመቻው በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት በየወረዳው የለይቶ ማቆያ ህክምና መስጫ ተግባራት ከወዲሁ ሊዘጋጁ ይገባልም ነው ያሉት።
 
አያይዘውም በተለይም ህብረተሰቡ ወረርሽኙን ለመቀነስ እና ለመቆጣጠር የፊት ጭንብል ማድረግ እንዲሁም እርቀትን መጠበቅ እና እጅን በአግባቡ በተደጋጋሚ መታጠብ፣ አስገዳጅ ካልሆነ በቀር በቤት መቆየትን ሁሉም ህብረተሰብ ሊተገብረው የሚገባ ተግባር መሆን አለበት ብለዋል።
 
ህብረተሰቡ በ”መ” ህጎች ዙሪያ ማለትም “መታጠብ”፣ “መሸፈን”፣ “መራራቅ” እና “መቆየት” በመተግበር የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
 
ከዚያም ባለፈ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነው የምርመራ እና የመከላከል ዘመቻ የተሳካ እንዲሆን የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና እገዛ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በመጠቆም ፣በዚህ ዘመቻ መገናኛ ብዙሃን እና የጥበብ ሰዎች የማስተማር ተግባራቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ማለታቸውን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.