Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሳሰቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥንቃቄ ማጠናከር አለበት- ዶ/ር ሊያ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት አሳሰቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አሳሰቡ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በሀገሪቱ ባለው የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ሁኔታ ዙሪያ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው በሀገሪቱ  የኮሮና ቫይረስ ስርጭት እስከትላንት ባለው ሁኔታ በተደረገው የ294 ሺህ የላብራቶሪ ምርመራዎች  ወደ 8 ሺህ ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ገልፀዋል።

ወረርሽኙ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የመጀመርያዎቹን 1 ሺህ ሰዎች ለማግኘት የፈጀበት ቀን 79 ሲሆን፥ ቀጣይ 1 ሺህ ሰዎችን ለማግኘት ግን ወደ 9 ቀን ብቻ ነው የወሰደው ብለዋል።

ይህም አሁን ባለው ደረጃ የወረርሽኙ ሁኔታ እየጨመረ ስለመምጣቱ ያሳያል ነው ያሉት።

የወረርሽኙ ሁኔታ በዚያ ልክ እየጨመረ ቢሆንም የሚያገግሙ ሰዎች ቁጥር ከፍ ማለቱም በመልካም የሚታይ ነው ብለዋል።

በወረርሽኙ ምክንያት የሚመዘገበው የሞት ቁጥርም ከሌሎቹ ሀገራት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ የሚባል እንዳልሆነ የገለፁት ዶክተር ሊያ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው 4 ነጥብ 4 በመቶ የሞት ምጣኔ ጋር ሲተያይ በጣም ከፍተኛ እንዳልሆነ ያሳያል ብለዋል።

ይህ ግን ቁጥሩ ይህ ብቻ ነው ማለት እንዳልሆነም ነው የተናገሩት።

ይህ የሚያሳየው እስካሁን ባለው የሞት መጠን እና የታማሚዎች ቁጥር መጨመር ወረርሽኙ እየጨመረ መምጣቱን ነው ሲሉ፤ ቀጣይ ወዴት ሊሄድ ይችላል የሚለውንም የተለያዩ ሳይንሳዊ ትንበያዎች እየተሰሩ የሚታይ ይሆናል ብለዋል።

ከፍተኛ ጭማሬውም መውረድ የሚጀምረው ከወራት በሁዋላ ሊሆን እንደሚችል ነው የገለፁት።

ስለዚህም እንደመንግስትም ሆነ እንደማህበረሰብ የሚሰሩ የጥንቃቄ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.