Fana: At a Speed of Life!

የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጣር በወጣ መመሪያ ቁጥር 30/2013 የተከለከሉ ተግባራትና የተጣሉ ግዴታዎች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና የሚያስከትለው ጉዳት ለመቀነስ አዲስ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጸድቆ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ዐቃቤ የተመዘገበው መመሪያ ቁጥር 30/2013 የወጣበት ዋናዉ ምክንያት ስለሚወሰዱ ክልከላዎች እና ግዴታዎች በህግ መወሰን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።

በመመሪያው የተከለከሉ ተግባራት

አካላዊ ንክኪና ተጓዦች፦ ማንኛውም ኮቪድ-19 ያለበት ሰው ቫይረሱ እንዳለበት እያወቀ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት፣ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ወይም ቫይረሱ ወደ ሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ በሚችልበት ሁኔታ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት፣ ማንኛውም ሰው ለሰላምታና ሌላ ለማንኛውም አላማ በእጅ መጨባበጥ፣ ሆነ ብሎ የእርስ በእርስ አካላዊ ንክኪ ማድረግ የተከለከለ ነው።

የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ፦ ማንኛውም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ቀሪ መሆኑ እስከሚወሰንበት ጊዜ ድረስ ከመኖርያ ቤት ውጪ በማንኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርግ መገኘት ወይም መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን ዕድሜያቸው ከስድስት አመት በታች የሆነ ህጻናት ወይም በማሰረጃ የተረጋገጠ የመተንፈሻ አካላት ወይም መሰል ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ይህ ድንጋጌ ተፈፃሚ አይሆንም።

በመንግስታዊ እና የግል ተቋም፦ በማንኛውም መንግስታዊ እና የግል ተቋም ሰራተኞች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የተከለከለ ነው።

ተገልጋዮች በሚቀመጡበት ጊዜም ይሁን በማንኛዉም አኳኋን አገልግሎቱ ሲያገኙ ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ተጠጋግተው እና የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ወይም በአንድ ጠረጴዛ ከሶስት ተገልጋዮች በላይ እንዲቀመጡ ማድረግ የተከለከለ ነው ሲሆን፥ ማንኛውም የንግድ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ ቀሪ መሆኑ ካልተወሰነ በስተቀር አፍና አፍንጫውን ላልሸፈነ ሰው አገልግሎት መስጠት የተከለከለ ነው።

ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ስፍራዎች፦ በክፍት ገበያዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ ቦታዎች፣ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎችና ሌሎች ህዝብ በሚበዛባቸው መሰል አካባቢዎች ከሁለት የአዋቂ እርምጃ በታች ርቀት መቆምም ሆነ መቀመጥ የተከለከለ ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አለም አቀፍ ኤርፖርቶችን በተመለከተ አለም አቀፍ ሲቪል አቪየሽን ድርጅት፤ አለምአቀፍ የአየር መንገዶች ማህበር እንዲሁም የአለም ኤርፖርት ድርጅት የሚያወጧቸውን መሰፈርቶች ባገናዘበ መልኩ በዘርፉ በሚወጡ መመሪያዎች መሰረት የሚከናወን ይሆናል።

የትህምርት ተቋማት፦ ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግስት ትምህርት ቤት የፊትለፊት ትምህርት መስጠት መጀመር እንደሚቻል ሳይወሰን እንዲሁም ትምህርት የሚሰጥበትን ሁኔታ ወይም አጠቃላይ የመማር ማስተማር ስራውን በተመለከተ በመመሪያ የሚወጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳያከብር ወይም ሌሎች ዝርዝር የትምህርት አሰጣጥ ስታንዳርዶችን ሳይከተል ትምህርት መስጠት የተከለከለ ነው።

ማንኛውም የግልም ሆነ የመንግስት ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርሲቲ የፊትለፊት ትምህርት መስጠት መጀመር እንደሚቻል ሳይወሰን እንዲሁም የሚሰጥበትን ሁኔታ ወይም አጠቃላይ የመማር ማስተማር ስራውን በተመለከተ በመመሪያ የሚወጡ የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳያከብር ወይም ሌሎች ዝርዝር የትምህርት አሰጣጥ ስታንዳርዶችን ሳይከተል ትምህርት መስጠት የተከለከለ ነው።

በሌላ በኩል ማንኛውም የህጻናት ማቆያ ማዕከል አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል ሳይወሰን እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጥበት ሁኔታ በተመለከተ በመመሪያ የሚወጡ ሊወሰዱ የሚገባቸው የጥንቃቄ እርምጃዎችን ሳያከብር አገልግሎት መስጠት አይችልም።

መመሪያው በግለሰቦች እና በተቋማት ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

በግለሰቦች ላይ የተጣሉ ግዴታዎች፦

በመመሪያዉ አንቀፅ 5 ላይ ማንኛውም ኮቪድ 19 በሽታአለብኝ ብሎ እራሱን የሚጠረጥር ሰው ለሚመለከተው አካል ሪፖርት በማድረግ የመመርመርና ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይተላፍ አስፈላጊውን ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡

በተጨማሪም በሽታው አለበት ተብሎ የሚጠረጠር ሰው ሰለመኖሩ የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ለጤና ሚኒስቴር፣ ለኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት፣ በአቅራቢያው ለሚገኙ የጤና ተቋም ወይም ባለሞያ የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡

አገልግሎት ሰጪ በሆኑ የመንግስትና የግል ተቋም ላይ  የተጣሉ ግዴታዎች፦

ማንኛውም አገልግሎት የሚሰጥ የመንግስታዊ እና የግል ተቋም አገልግሎቱን ለማግኘት ወደ ተቋሙ ለሚመጡ ተገልጋዮች ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳሶችን የማቅረብ፣ ተገልጋዮች ሁለት የአዋቂ እርምጃ ተራርቀው የሚቆሙበትን ቦታ ምልክት የማድረግ እና ተገልጋዮች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ተጥሎበታል።

በተጨማሪም ለሰራተኞች ስለበሽታው አስፈላጊውን መረጃ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማድረስ፣ በመግቢያና መውጫ በሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቦታዎች በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮችን የማዘጋጀት፣ የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችን መተግበራቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው።

የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

ሀገር አቀፍም ሆነ የከተማ ውስጥ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ሰው በህግ ከሚወሰነው የመጫን አቅም ልክ ሰዎችን የመጫን፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ያላደረጉ ሰዎችን አገልግሎት አለመስጠት፣ መስኮቶችን በመክፈት በተሽከርካሪው ውስጥ በቂ የአየር ዝውርውር እንዲኖር የማድረግ እና በዘርፉ በመመሪያ የሚወጡ ሌሎች መወሰድ የሚገባቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች በመተግበር አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አለበት።

የኮንስትራክሽን አሰሪዎች ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት አሰሪዎች በግንባታ ሳይቶች ላይ አስፈላጊውን ንጽህና ለመጠበቅ የሚረዱ እንደ ውሃ፣ ሳሙና፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ፣ ሳኒታይዘር ወይንም አልኮል፣ የሙቀት መለኪያ መሳሪያ እንዲሁም የጸረ ተህዋሲያን ግብዓት የማቅረብ ወይንም የሟሟላት፣ ሰራተኞች በተቻለ መጠን ርቀታቸው ጠብቀው እንዲሰሩ የማድረግ፣ እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመከላከል፣ ዝግጁነት ለማረጋገጥና ምላሽ አሰጣጥ ሁኔታን በተመለከተ በዘርፉ በመመሪያ የሚወሰኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች የማክበር እና የማስከበር ግዴታዎች አለባቸው።

የሆቴልና ቱሪዝም አሰሪዎች ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

ማንኛውም በሆቴል፣ በአስጎብኚነት እና በሌሎችም የቱሪዝም መስክ የተሰማሩ ተቋማት በሰራተኞቻቸው እና ተገልጋዮቻቸው መካከል ሁለት የአዋቂ እርምጃ ወይም የሁለት ሜትር ርቀት እንዲኖር የማድረግ፣ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን የመቆጣጠር፣ በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮችን የማዘጋጀት፣ ለሰራተኞቻቸው የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ እንዲሁም የቱሪዝም አገልግሎት በሚሰጡበት ወቅት ዘርፉ በመመሪያ የሚያስቀምጣቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

የኢንዱስትሪ እና ምርት መስክ የተሰማሩ መንግስታዊ እና የግል ተቋማት ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

ለሰራተኞቻቸው ስለበሽታው አስፈላጊውን መረጃ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የማድረስ፣ በመግቢያና መውጫ በሮችና ሌሎች አስፈላጊ ቦታዎች በሽታውን ለመከላከል የሚያስችሉ አስፈላጊ ነገሮችን ማዘጋጀት፣ የስራ ቦታዎችን በቂ የአየር ዝውውር ሊኖርበት በሚችል መልኩ የማደራጀት፣የበሽታውን ስርጭት ለመግታት የሚረዱ የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን የማቅረብ፣ ሰራተኞች የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረጋቸውን እና ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎችንመተግበራቸውን የማረጋገጥ፣ እንዲሁም ሌሎች ዘርፉ በመመሪያ የሚያስቀምጣቸውን የጥንቃቄ እርምጃዎች ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

በሁሉም ዘርፍ ያሉ ተቋማት ላይ የተጣሉ ግዴታዎች

ማናቸውም መንግስታዊም የሆነ የግል ተቋም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተጋላጭነትን ለመከላከል፣ ዝግጁነት ለማረጋገጥ እና ምላሽ አሰጣጥ ሁኔታን በተመለከተ በዘርፉ በመመሪያ የሚወሰኑ የጥንቃቄ እርምጃዎች የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት።

በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎችን እና ግዴታዎችን መጣስ የሚያስከትለው ቅጣት

በመመሪያው የተቀመጡ ክልከላዎች እና ግዴታዎች ተላላፊ በሽታን ለመከላከል እና ለመግታት የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎች አካል ሲሆኑ ክልከላዎቹን መተላለፍ እና ግዴታዎቹን አለመወጣት አግባብ ባለው የወንጀል ህግ እንደሚያስቀጣ በመመሪያው ተደንግጎ ይገኛል።

በዚህም መሰረት በወንጀል ህጉ አንቀፅ 522 ንዑስ አንቀፅ 1 ስር እንደተደነገገው ማንም ሰው ማለትም የተፈጥሮ ሰው ወይም በህግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ተላላፊ በሽታን ለመከላከል፣ ለመግታት ወይም ለማቆም በህግ የተደነገጉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን አስቦ የጣሰ እንደሆነ ከሁለት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል።

እንዲሁም ወንጀሉ የተፈፀመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከስድስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከሦስት ሺህ ብር የማይበልጥ መቀጮ መሆኑን አንቀፅ 522/2 እንደሚደነገግ ከጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.