Fana: At a Speed of Life!

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ ፣ጥቅምት 12 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገለፁ።

2 ሺህ 160 ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ግድብ በኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።

የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ÷ በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2025 ሃሀገር አቀፍ ደረጃ የሚገነባው ኢኮኖሚ 20 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያስፈልገው በስትራቴጂክ ዕቅድ መቀመጡን ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

ከዚህ አንጻር የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በሶስት ዓመት ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ግድቡ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የጊቤ ሶስት ውሃ የሚጠቀም በመሆኑ 6 ቢሊየን ኪዩቢክ ሊትር ውሃ ብቻ እንዲይዝ ተደርጎ እንደሚገነባም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ይህ ደግሞ ግድቡን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ዕድል ይሰጣል ነው ያሉት።

ግድቡ “በገበታ ለሀገር” የኮይሻ ፕሮጀክት መካተቱን ጠቅሰው÷ የግድቡ በፍጥነት መጠናቀቅ አካባቢውን የጎብኚዎች መዳረሻ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ መሆኑንም ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ የኮንትራት ስራዎች ተቆጣጣሪ አቶ ኢዩኤል ሰለሞንም በእስካሁን ሂደት የውሃውን ተፈጥሯዊ አቅጣጫ ማስቀየርን ጨምሮ መሰረታዊ የቁፋሮ ስራዎች መጠናቀቃቸውን ገልጸዋል።

የማስተንፈሻ ግንባታ ቁፋሮው ከግማሽ በላይ መጠናቀቁንም አክለዋል።

ዋናው ግድብና የኃይል ማመንጫው በተለያዩ ቦታዎች እንደሚገኙ የገለፁት አቶ እዩኤል ይህ ደግሞ አንደኛው ግንባታ ሌላኛውን ሳይጠብቅ በተመሳሳይ ጊዜ እንዲከናወኑ ዕድል ይሰጣል ብለዋል።

የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በጊቤ-ኦሞ ወንዝ ኮሪደር ከሚገኙ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አራተኛው ነው።

ለአራት ሺህ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረው የኮይሻ ኃይል ማመንጫ የግንባታ ስምምነቱ የተፈረመው በመጋቢት 2008 ዓ.ም ነው።

የፕሮጀክቱ አሁናዊ የግንባታ አፈፃፀም 39 በመቶ መድረሱንም ኢዜአ ዘግቧል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.