Fana: At a Speed of Life!

የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ተመረቀ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 7፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የወረታ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የመጀመሪያ ምዕራፍ ተመረቀ።

በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዲሁም የፌደራልና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎች ተገኝተዋል።

ከዚህ ባለፈም በገዳሪፍ ዋና አስተዳዳሪ ሜጀር ጀኔራል ነስረዲን አብዲ የተመራ ልዑክም በስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝቷል።

የወደቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የ3 ሄክታር ግንባታ በጠጠር ንጣፍ የተዘጋጀ የኮንቴነርና የተሽከርካሪ ማስተናገጃ ተርሚናል፣ 500 ሜትር ካሬ መጋዘን፣ የቢሮ ህንፃ፣ የመዳረሻ የውስጥ ለውስጥ መንገድ የጥበቃ ማማ እና የዙሪያ አጥር ያሟላ ነው።

በተጨማሪም የጥልቅ ውሃ ጉድጓድና የውሃ መፋሰሻ ስርዓት እንዲሁም መጠባበቂያ ጄኔሬተርን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እና ሌሎችም አስፈላጊ መሰረተ ልማቶች አሉት።

ወደቡ 75 ቶን ዕቃ መያዝ የሚችል መጋዝን ያለው ነው።

በቀጣይ ምዕራፎች በ20 ሄክታር መሬት ላይ የደረቅ ወደብ የሚገነባ ሲሆን፥ ሲጠናቀቅ እስከ 9 ሺህ 450 ኮንቴነሮችን ማስተናገድ ይችላል ተብሏል።

ከዚህ ባለፈም በዓመት 95 ሺህ 800 ኮንቴነሮችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው ታውቋል።

በርስቴ ፀጋዬ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.