Fana: At a Speed of Life!

የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመፍታት አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች እንዳይጓተቱ የወሰን ማስከበር ችግሮችን በመፍታት ረገድ አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት እንዳለበት ተገለፀ፡፡
ከክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በወሰን ማስከበር ችግሮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ ላይ የተገኙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ አመራሩ ወደ ልማት ተነሽዎች በመቅረብና ችግራቸውን በወቅቱ በመፍታት የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የክፍለ ከተማ አመራሮች በበኩላቸው ከምትክ ቦታ፣ ከቅያሬ ቤት፣ ከፍርድ ቤት እግድና ከመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ጋር በተያያዘ ችግሮች እንደሚያጋጥማቸው ገልፀዋል፡፡
ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ችግሮችም በከተማ አስተዳደሩ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጥባቸው ጠይቀዋል፡፡
አቶ ዣንጥራር ለውሳኔ አሰጣጥ እንዲያመች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ጉዳዮችን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለይተው ለከተማ አስተዳደሩ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ የወሰን ማስከበር ስራዎችን በቁርጠኝነትና በትኩረት መስራት ከተቻለ የመንገድ ፕሮጀክቶችን በወቅቱ ማጠናቀቅ ይቻላል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.