Fana: At a Speed of Life!

በመስኖ ልማት ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም በስፋት እየተሠራ ነው – ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በመስኖ ልማት ዘርፍም የኦሮሚያ ክልልን እምቅ አቅም ለመጠቀም በስፋት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

ውይይቱ ትኩረቱን ያደረገው በክልሉ ውስጥ በመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ በመስኖና የተፋሰስ ልማት እንዲሁም በኢነርጂ ዘርፎች እየተካሄዱ ባሉ የልማት ሥራዎች ዙርያ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በውይይቱ መግቢያ ላይም የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መድረኩ ያስፈለገው የሥራ ግንኙነትን ለማጠናከር፣ እንደ ሀገር የሚሠሩ ሥራዎችን ልማት ለማፋጠን ነው ብለዋል፡፡

እንዲሁም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በክልሉ የሚሠራቸውን የልማት ሥራዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች በክልሉ አመራሮች በኩል ግንዛቤ እንዲያዝባቸው ለማድረግ፣ልማቱን ማፋጠን ያላስቻሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታትና መፍትሔዎችን በጋራ ለማመንጨት እንዲሁም የጋራ ውጤታማነት፣የክትትልና ግምገማ መሠረት ለመጣል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በመጪዎቹ 10 ዓመታት ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች ሙሉ በሙሉ የንጹህ መጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እቅድ ተይዞ እየተሠራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በክልሉ እየተካሄዱ ባሉ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ የመስኖ ልማትና ኢነርጂ ዘርፍ ፕሮጀክቶች ዙርያ እያጋጠሙ ያሉና የክልሉን ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚፈልጉ ሥራዎችን በተመለከተ የዘርፉ ሚኒስትር ዴኤታዎች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የማቺንግ ፈንድ፣ ከካሣ ክፍያና በልማት ምክንያት ከቦታቸው በሚነሱ የኅብረተሰብ ክፍሎች  እንዲሁም ከፕሮጀክቶች መዘግየት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙርያ በሰፊው ምክክር ተደርጓል፡፡

በክልሉ የዘርፉን የግንባታ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኙ ተቋራጮችና አማካሪዎች የተሳተፉ ሲሆን እያከናወኗቸው ስላሉት ፕሮጀክቶችን ስላጋጠሟቸው ተግዳሮቶች እንዲሁም በክልሉ መንግሥት ሊፈቱ ይገባሉ ያሏቸውን ጉዳዮች አቅርበዋል፡፡

የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደር አቶ ሽመልስ አብዲሳ መሰል ውይይቶች ባለፈው ዓመትም መደረጋቸውን አስታውሰው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ በክልሉ የሚያካሂዷቸውን የልማት ሥራዎች ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበርና በቡድን መንፈስ ለመሥራት እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ከማቺንግ ፈንድ ጋር በተያይዞ፣በልማት ሥራዎች ምክንያት ከመኖሪያቸው የሚነሱ የህብረተሰብ ክፍሎችና የካሣ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ ክልሉ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ዘርፎች የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው ትልቅ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በክልሉ ሰሞኑን ይፋ በሆነው ገዳ የኢኮኖሚ ከተማ ዙሪያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ በቀጣይ ዓመታት በዕቅዶቻቸው እንዲያካትቱት ጠይቀዋል፡፡

በውይይት መርሐ ግብሩ ላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ ኮሚሽነሮች፣ዳይሬክቶሮች፣ሥራ አስፈጻሚዎች እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.