Fana: At a Speed of Life!

የውጪ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በግብርናና ቱሪዝም ዘርፍ እንዲሰማሩ መልካም ዕድሎችን በስፋት ማስተዋወቅ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኖርዲክ ትሬዲንግና አጋር ድርጅቶቹ “የኢትዮጵያ ስጦታዎች” በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ዓለም አቀፍ የዝግጅት መርሐ ግብርን ዘርግቶ ይፋ አድርጓል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ እንደተናገሩት፥ ዝግጅቱ ኢትዮጵያ ያላትን ባህል፣ ቅርስና ትውፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ፣ ገጽታ በመገንባቱና በማደሱ ረገድ የበኩሉን ሚና የሚጫወት በመሆኑ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ መለያ የሆነውን ጤፍ፣ እንጀራንና ባህላዊ ምግቦችን መሠረት አድርጎ፥ ትውፊታችንን፣ የቡና ስርዓታችንን እና ሌሎች የኢትዮጵያን መለያና መገለጫዎች ላይ በማተኮር በተለያዩ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የመካከለኛ ምስራቅ ሀገራት ለማስተዋወቅ ያቀደ መሆኑ ኢትዮጵያ ያላትን ዘርፈ ብዙና ወጥ ስጦታዎች ለዓለም ለማስተዋወቅ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ፥ ፌስቲቫሉ የውጪ ኩባንያዎችና ባለሃብቶች በግብርናው ዘርፍ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ታግዘው በኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የማነቃቃት ስራ የሚያከናውን፣ የሀገርን ፈጣን እድገትና ወቅታዊ ሁኔታ ለውጭ ሀገራት በተጨባጭ በማስተዋወቅ የገፅታ ግንባታ ስራም የሚሰራ ነው ብለዋል።

በዘርፉ አዳዲስ ባለሃብቶችም ተሰማርተው ራሳቸውንና ሃገራቸውን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት እድልን እንደሚፈጥርም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

የመጀመሪያ ዙር የኢትዮጵያ ስጦታዎች ፌስቲቫል በመጪዎቹ ወራት በጀርመንና በኔዘርላንድስ እንደሚካሄድ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.