Fana: At a Speed of Life!

የውጭ አገራት ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014(ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ አገራት ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የሚተገበር የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አስታወቀ።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ቁጥጥር ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ አገራት ክፍት ለማድረግ የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ መሆኑን ጠቁመው÷ ዘርፉ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆን በተወሰኑ ተዋናዮች ብቻ ታጥሮ የቆየው የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል ብለዋል።

በዚህም መሰረት ባንኮቹ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ዘርፉ የሚመራበት የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው÷ የባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባትም ለእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የውጭ ምንዛሪ ፍሰትን ለመጨመር፣ የብድር አገልግሎትን ለማስፋትና ሌሎችም ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት አብራርተዋል፡፡

በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ በፋይናንስ መደገፍና አዳዲስ አሠራሮችን ያመጣሉ ተብሎም ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

የባንኮቹ ወደ አገር ውስጥ መግባት ከሚኖረው ጠቀሜታ ባለፈ በሂደቱ ሊያስከትል የሚችለውን ስጋት ሊቀንስ የሚችል የሕግ ማዕቀፍና የአሠራር ሥርዓት እየተዘጋጀ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአገር ውሰጥ ባንኮች ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሰው ኃይል፣ በአቅም እና በቴክኖሎጂ ጭምር በመጎልበት ለውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ ያስገነዘቡት ዳይሬክተሩ÷ የተጠናከረና የተደራጀ ባንክ ከመፍጠር አንጻር በራሳቸው ፈቃድ አንዱ ከሌላው ጋር የመዋሃድ አማራጭን መከተልም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የሕግ ማዕቀፉ በሚፈልገው ልክ ጠንካራ፣ ብቁና አስፈላጊውን መስፈርት የማያሟሉ ባንኮች ካጋጠሙ በመዋሃድ መሥራት በአማራጭነት የሚወሰድ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.