Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ በሮም ከሚገኙ ዓለም ዓቀፍ ድርጅት ሃላፊዎች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 19፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በጣሊያን ጉብኝታቸው ተቀማጭነታቸው ሮም ከሆኑ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች የሥራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
 
ሚኒስትሩ ከዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ኩ ዶንገዩ፣ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈፃሚ ዴቪድ ባስሌይ እና ከዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሁንግቦ ጋር ነው የተወያዩት።
 
በውይይታቸውም ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ የጀመሯቸውን የልማት ፕሮጀክቶች ማጠናከር በሚችሉባቸው መንገዶች ዙሪያ እና ከሀገሪቱ ጋር ያላቸውን ዘርፈ ብዙ ትብብር አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ መክረዋል።
 
አቶ ገዱ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ስራ አስፈፃሚ ከዴቪድ ባስሌይ ጋር በነበራቸው ውይይት ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
 
ከዓለም እርሻና ምግብ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ኩ ዶንገዩ ጋርም ድርጅቱ በሀገሪቱ የተከሰተውን የበርሃ አንበጣ ለመከላከል ለሚሰሩ ስራዎች እና ለኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን የሚደረጉ ድጋፎች እና ትብብሮች በሚጠናከሩበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።
 
እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት ፈንድ ፕሬዚዳንት ጊልበርት ሁንግቦ ጋር ተቋሙ ለግብርናው ዘርፍ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ አጠናክሮ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
 
ሶስቱም ሃላፊዎች በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው ለውጥ አድናቆት እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን፥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
 
አቶ ገዱ ድርጅቶቹ እስካሁን ላደረጉት እና እና አሁንም ለሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ትብብር የተቋማቱን ሃላፊዎች በማመስገን ቀጣይ የክትትል ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.