Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ጋር ተወያዩ።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ የተመራ የልዑካን ቡድን በጎርፍ ለተጎዱ ሱዳናዊያን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ለማድረግ ካርቱም ገብቷል።
በልኡካን በድኑ ውስጥ የኢፌዴሪ መከላከያ ኤታማጆር ሹም ጀነራል አደም መሃመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተካታውበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅትም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተላከ መልዕክት ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ እና ለሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን አድርሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ሱዳናዊያንን ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከሱዳን ህዝብና መንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመልዕክታቸው ላይ መግለፃቸውን ሱና የዜና ወኪል ዘግቧል።
ድጋፉ በጎርፍ ለተጎዱ ሱዳናዊያን አገልግሎት የሚውል የተለያየ መጠን ያለው የእለት ደራሽ አልሚ ምግብ፣ ዱቄት፣ መድሃኒት፣ ስኳር፣ የአልጋ አጎበር እና ሌሎች ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን መሆኑን አቶ ገዱ በዚህ ወቅት ገልፀዋል።
ከዚህ ባለፈ ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሌተናል ጄነራል አብዱል ፈታህ አልቡርሃን ጋር ከሁለቱ ሀገራት ድንበር በተያያዘ ውይይት ያደረጉ ሲሆን የሚፈጠሩ ችግሮችንም በቅንጅት ለመፍታት ይሰራል ተብሏል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ተጠባባቂ ሚኒስትር ኦማር ቀመር-አልዲን እስማኤል የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.