Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለ125ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለ125ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ፡፡

ለአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን እንኳን አደረሳቹሁ!

የአድዋ ድል 125 ዓመታት ወደኋላ ተሻግሮ በእናት ሃገር ልጆች ብርቱ ተጋድሎ እና ታላቅ መስዕዋትነት የተመዘገበ የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው።
ወራሪ ጠላት ሃገራችንን በቅኝ የማሳደር የተንጠራራ ምኞት ተከትሎ፤ በአፀፋው በተሰጠ ጀብዳዊ ምላሽ የተቀዳጀነው አንፀባራቂ የነፃነት ድል ነው።

ይህ ድል ሁሌም በትውልድ ልቦና ጎልቶ የሚታወስ ከመሆኑ ባሻገር በውስጡ ትልቅ ትርጉም ያነገበ በመሆኑ፤ እነሆ 125ኛ ዓመቱን በልዩ ትኩረት እና አፅንዖት ለማክበር በቅተናል።

በተለይ ዘንድሮ የድሉን ቀን ስናከብር ለአሁኑ ትውልድ ደማቅ የታሪክ ፈለግ የምናሰርፅበት መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል።
ከሁሉ በላይ የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች ነፃነት ተምሳሌታዊ ምልክት በመሆን እስከዛሬ ድረስ ዘልቋል፤ ወደፊትም የኩራት ምንጭ ሆኖ እያገለገለ በክብር ይዘልቃል።

ይህ ደማቅ የታሪክ ፈለግ በውስጡ ያዘለው ተሻጋሪ ትርጉም በእናት ምድር ቅጥር ብቻ የተቀነበበ ባለመሆኑ፤ የድሉን ቀን በድምቀት ስለማክበራችን ምክያታዊነቱን በእጅጉ ያፀናል።

የአድዋ ድል የቀደመው ትውልድ የጀብድነት ጥግ እና የጀግንነት ከፍታ የተገለጠበት አንፀባራቂ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑን ለትውልዱ በሚገባ ማስጨበጥ ይጠይቃል።

በዘመን ቅብብሎሽ የወረስነውን የጀግንነት ከፍታ በጥበብ መመልከት እና በጥንቃቄ ማስተዋል ይጠይቃል፤ ደግሞም ይገባል።

ትውልዱ እንደቀደሙት አባቶቻችን አንድነቱን አጥብቆ፤ ራስን ከሃገር በታች በማድረግ ዘመኑ ለሚጠይቀው ትግል በፅናት የመሰለፍ እና ድል የመንሳት እሴት ያጋራል።

እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ መታገል እና በጋራ ድል መቀዳጀት ልምድ የሚያጥረን ህዝቦች አለመሆናችን፤ የአድዋ ድል ትልቅ ታሪካዊ ማሳያ ነው።

በቀደመው ትውልድ የተቀዳጀነው ታሪካዊ ድል በዘመን ቅብብሎሽ ለተከተለው ትውልድ የፈጠረውን ወርቃማ ዕድል ውሃ ልኩን ጠብቆ ማክበር ይገባል።

በአሁኑ ጊዜ ሃገራችን ከገጠሟት ገፀ ብዙ ፈተናዎች በጥንቃቄ እና በአስተውሎት ለማሻግር፤ እንዲሁም የታፈረች እና የተከበረች ሃገር ለመጪው ትውልድ ለማወርስ በዚህ አጋጣሚ ትውልዱን የቀደሙ አባቶቻችንን ታሪክ በተግባር እንዲደግም አደራ ለማለት እወዳለሁ!!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.