Fana: At a Speed of Life!

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከፖርቹጋል አቻቸው ቴሬዛ ሪቤይሮ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከፖርቹጋል አቻቸው ቴሬዛ ሪቤይሮ ጋር በዙም የሁለቱን አገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ።

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የሁለቱ አገራት ግንኙነት ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ መሆኑን በማስታውስ፤ ፖርቹጋል የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆና በመመረጧ የተሰማውን ደስታ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ፖርቱጋል የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በመሆን በምትቆይበት ወቅት ከዚህ ቀደም የነበሩ የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መስራቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደር ሬድዋን አንስተዋል።

የአውሮፓ ህብረት እና የአፍሪካ ህብረት ባላቸው ጠንካራ ትብብር የስደተኞችን ጉዳይ እልባት ለመስጠት ጥረታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ እምነታቸው መሆኑንም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገልጸዋል።

ሁለቱ አህጉሮች የህዝቦቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ ልማት፣ በኢንስትመንት እና በንግድ ግንኙነታቸውን አሁን ካለበት ይበልጥ ማጠናከር እንዳለባቸውም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አሳስበዋል።

ቴሬዛ ሪቤይሮ በበኩላቸው የኢትዮጵያ 2013 አዲስ ዓመት ለህዝቦቿ የስኬት ዘመን እንዲሆን መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።

ፖርቹጋል ከኢትዮጵያ እና ከአፍሪካ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትርጉም እንደምትሰጥም ቴሬዛ ሪቤይሮ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።

ፓርቹጋል በአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዘመኗ ከአፍሪካ ጋር በትብብር ለመስራት ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያና ፖርቱጋል የፖለቲካ ምክክርን ጨምሮ ሌሎች መድረኮችን በስፋት በመጠቀም ትብብራቸውን ይበልጥ ማስፋት እንደሚጠበቅባቸውም ቴሬዛ ሪቤይሮ አሳስበዋል።

ሁለቱ አገራት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በበጋራ ለመከላከልም በትብብር መስራታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቴሬዛ ሪቤይሮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.