Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ሀገራት መሪዎች ለኮሮናቫይረስ ክትባት ስራ ከ8 ቢሊየን ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም ሀገራት መሪዎች ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ለሚደረገው ጥረት ከ8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለፀ።

በአውሮፓ ህብረት አስተባባሪነት ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት በሚደረገው ጥረት ዙሪያ በኢንተርኔት አማካኝነት በኦን ላይን በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከ40 በላይ ሀገራት መሪዎች መሳተፋቸው ተነግሯል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኦርሱላ ቮን ዴር ላይን፥ ሀገራት የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ያሳዩት ተነሳሽነት ዓለም አቀፋዊ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።

በአጠቃላይ ከተባበሩት መንግስታት በተጨማሪ ከ30 በላይ ሀገራት ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት ለሚደረገው ጥረት የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እና ኖርዌይ እያንዳንዳቸው የ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን፥ ጀርመን፣ ጃፓን እና ሳዑዲ አረቢያ እያንዳንዳቸው ከ800 ሚሊየን ዶላር በላይ እንዲሁም ፈረንሳይ 500 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አድርገዋል።

አሜሪካ እና ሩሲያ በኦንላይን ስብሰባው ላይ እንዳልተሳተፉ የተገለፀ ሲሆን፥ የኮሮና ቫይረስ መነሻ የሆነችው ቻይና በአውሮፓ ህብረት አምባሳደሯ በኩል ብትሳተፍም የገንዘብ ድጋፍ ስለማድረጓ አልተገለፀም።

ከመንግስታት በተጨማሪም ግለሰቦችም ድጋፍ አደርገዋል ያሉት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንቷ፤ በዚህም የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኟ ማዶና የ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጓን አስታውቅዋል።

የብሪታኒያው ፕሬዚዳንት ቦሮስ ጆንሰንም ሀገራቸው 388 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ እንደምታደርግ በስብሰባው ላይ ገልፀዋል።

ለኮሮናቫይረስ ክትባት ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ከተዋጣው ገንዘብ ውስጥ 4 ነጥን 4 ቢሊየን ዶላር ለክትባት ስራ የሚውል ሲሆን፥ 2 ቢሊየን ዶላር በህክምናው ዙሪያ ለሚደረግ ምርምር እንዲሁም 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ደግሞ የምርመራ ስራን ለማጠናከር የሚልው መሆኑን የአውሮፓ ህብረት አስታውቋል።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.