Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ንግድ ድርጅት የአውሮፓ ህብረት በአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ መጣል እንደሚችል አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የዓለም የንግድ ድርጅት የአውሮፓ ህብረት 4 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ የአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ መጣል እንደሚችል አስታወቀ፡፡
 
ህብረቱ ቀረጥ የሚጥለው አሜሪካ ለአውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ የገንዘብ ድጋፍ በማድረጓ ነው ተብሏል፡፡
 
ድጋፉን ተከትሎም የቦይንግ የንግድ ተቀናቃኝ የሆነው የአውሮፓው ኤር ባስ ተጽዕኖ ደርሶበታል ነው የተባለው፡፡
 
ኤር ባስ ሽያጩ መቀነሱን እንዲሁም የወጪና የገቢ ንግዱም መቀዛቀዙን የዓለም የንግድ ድርጅት ጠቅሷል፡፡
 
ውሳኔውን ተከትሎ የአሜሪካ የንግድ ተወካይ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል፡፡
 
ተወካዩ ሮበርት ላይቲዘር አውሮፓ በአሜሪካ ምርቶች ላይ ቀረጥ ለመጣል ህጋዊ መሰረት የላትም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
 
ህብረቱ በበኩሉ ከአሜሪካ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ውይይት እንደሚያካሂድ ገልጾ ስምምነት ላይ የማይደርሱ ከሆነ የአውሮፓን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሚዛናዊ ውሳኔ እንደሚያሳላልፍ አስታውቋል፡፡
 
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአውሮፓ ሃገራት ለኤር ባስ ድጋፍ አድርገዋል በሚል አሜሪካ መክሰሷ ይታወቃል፡፡
 
ይህንንም ተከትሎ የዓለም የንግድ ድርጅት አሜሪካ 7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር በሚያወጡ የአውሮፓ ምርቶች ላይ ቀረጥ እንድትጥል መፍቀዱም የሚታወስ ነው፡፡
 
 
ምንጭ፡- ሺንዋ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.