Fana: At a Speed of Life!

የዩክሬንን እህል ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሩሲያ ጋር ስምምነት መደረሱን ቱርክ አስታወቀች

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ቱርክ በጥቁር ባሕር የዩክሬንን እህል ለዓለም ገበያ ለማቅረብ ከሩሲያ ጋር ስምምነት መደረሱን አስታወቀች።

የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም በዛሬው እለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በተገኙበት በሩሲያ እና ዩክሬን ተወካዮች መካከል በኢስታንቡል የሰነድ የፊርማ ሥነ ስርአት እንደሚኖርም ተገልጿል።

የዩክሬን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትም የሀገሪቱ የጥሬጥሬ ምርት ከጥቁር ባሕር ተነስቶ ለዓለም ገበያ እንዲደርስ የሚያስችል የስምምነት ሰነድ በዛሬው እለት ሊፈረም እንደሚችል አረጋግጧል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪም ዩክሬን “ከወደቦች መከፈት ጋር የተያያዙ” ዜናዎችን ትጠብቃለች ብለዋል።

ለሚፈረመው የስምምነት ሰነድ ቅርብ የሆኑ አንድ የዩክሬን የፓርላማ አባል ግን ከስምምነት ሰነዱ ጋር ተያይዞ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በስምምነቱ መሰረት ጥራጥሬ የጫኑ የዩክሬን መርከቦች ያለምንም ገደብ እንዲንቀሳቀሱ ሲፈቀድላቸው ሩሲያም መርከቦቹ እህል ጭነው በሚጓዙበት ወቅት የተኩስ አቁም ታደርጋለች።

ከዩክሬን ባለፈም ሩሲያም የጥራጥሬ እና ማዳበሪያ ምርቶቿን በጥቁር ባሕር በኩል ለዓለም ገበያ የምታቀርብበትን መንገድ ማሳለጥም የስምምነቱ አካል መሆኑም ነው የተገለጸው።

ቱርክም በተመድ ድጋፍ እየተደረገላት በአካባቢው የመሳሪያ ዝውውር እንዳይኖር በሚል ከሩሲያ በኩል የተነሳውን ስጋት ለመቅረፍ በመርከቦቹ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ታደርጋለች ነው የተባለው።

የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት ካለፈው የካቲት ወር ጀምሮ የጥራጥሬ ምርት ለዓለም ገበያ እየቀረበ አይደለም።

ለዚህ ደግሞ ዩክሬን ሩሲያ የጥቁር ባሕር ወደቦችን ዘግታብኛለች በሚል ስትኮንን በአንጻሩ ሩሲያ ውንጀላውን ታስተባብላለች።

በአካባቢው ካለው የባሕር ትራንስፖርት መስተጓጎል ጋር በተያያዘም አሁን ላይ ወደ 20 ሚሊየን ቶን የሚጠጋ የጥራጥሬ ምርት በኦዴሳ ሲሎስ ተከማችቶ እንደሚገኝ ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.