Fana: At a Speed of Life!

የደሴ ከተማና አካባቢዋን ሰላም የሚያውኩ ሰርጐ ገቦችን ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ የከተማ አስተዳደሩ ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “አካባቢያችንን ከሰርጐ ገቦችና የማህበረሰቡን ሰላም ከሚያውኩ አካላት ነቅቶ መጠበቅና አንድነትን ማጠናከር ይገባል” ሲሉ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ አሳሰቡ፡፡
ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ “ካለፉት ጊዜያት የተማርነው በውስጣችን ሆነው ህብረተሰባችንን እርስ በርስ እንዳይተማመን የተለያዩ አጀንዳዎችን እየፈበረኩ ሰላም የሚያሳጡንን አላማ ተቀብሎ ማስተናገድ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአንጻሩ የአሸባሪው ህወሓት ዳግም ወረራ በመንግስት ዝግጅትም ሆነ በማህበረሰቡ ንቃት የሚታሰብ አይደለም ነው ያሉት፡፡
የተበታተነ የጸጥታ መዋቅር ለሌሎች መጠቀሚያ የመሆን እድል ስለሚኖረው ተጠያቂነት ባለው፣ በሚታወቅና በዕዝ ሰንሰለት በሚመራ መዋቅር ውስጥ ሆኖ እና መሳሪያን አስመዝግቦ የአካባቢውን ሰላም ሁሉም ነቅቶ መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በተለይም ወጣቶች በዚህ ጊዜ ከመንግስት ጎን በመሆን የህወሓትንና ተላላኪዎቹን አላማ ማክሸፍ እንጂ በውሸትና አሉባልታ መታለል እንደሌለባቸው አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በተለያዩ ህገ ወጥ አካላት ላይ መንግስትና ከተማ አስተዳደሩ እየወሰዱት ያለውን እርምጃ እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአንድነት ናሁሰናይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.