Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ኮሚቴ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራት በማከናወን ላይ መሆኑን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 11፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ህዝበ ውሳኔ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቀጣዩ ግንቦት ወር ለሚካሄደው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የሚያስችሉ ተግባራትን በማከናወን ላይ መሆኑን ኮሚቴው አስታወቀ፡፡

ኮሚቴው ዛሬ ከኢፌዴሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ባካሄደው ውይይት ነው ስለህዝበ ውሳኔው ያሳወቀው፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ በላቸው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ባቀረቡት የክልልነት ጥያቄ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝቦች ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ውሳኔ ማስተላለፉንና ውሳኔውንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲያስፈፅም መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡

ህዝበ ውሳኔ አሰጣጡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወንና በቅድመ ህዝበ ውሳኔ፣ በህዝበ ውሳኔ አሰጣጥና ከድህረ ውሳኔ በኋላ የሚከናወኑ ተግባራትን በአግባቡ እንዲመራ ከ6 መዋቅሮች አምስት፣ አምስት በድምሩ 30 አባላት መመረጣቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 13ቱ አባላቱን በመወከል እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኮሚቴው የህዝበ ውሳኔ አሰጣጡ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን የራሱን ዕቅድ በማዘጋጀት አባላቱን ያወያየና ዕቅዱም የሁሉንም አባላት ይሁንታ ያገኘ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም በህገ-መንግስት ዝግጅት፣ በህዝብ ግንኙነት ስራ፣ በሎጎ፣ በባንዲራ፣ በቋንቋ፣ በልማት ዕቅድ ዝግጅት፣ ህዝበ ውሳኔው ከተካሄደ በኋላም በአካባቢው ካሉ ማህበረሰቦች ጋር በባህል እና ነባሩን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግራትን የሚያከናውኑ አምስት ግብረ ኃይሎችን በማቋቋም ወደ ስራ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው ኮሚቴው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት ጥያቄ ሰላማዊ የሆነ ህዝበ ውሳኔ እና ሽግግር እንዲኖር ለማስቻል የተዋቀረና የፌደራል አካላትን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ኮሚቴውም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጋር በትብብር እንደሚሰራም አስታውቀዋል፡፡

ኮሚቴው ቀሪ ስራዎችን በተሳካ ሁኔታ እንዲሰራ በምክር ቤቱ በኩል የቴክኒክና የባለሙያ ድጋፍ እንደሚደረግለትም አክለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ በቦርዱ በኩል ህዝበ ውሳኔው ከአጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫው ጋር ለማካሄድ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ህዝበ ውሳኔ ከመካሄዱ በፊት ለህዝቡ በቂ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ በህዝበ ውሳኔው ላይ ቅር የሚሰኙ አካላትን የማወያየትና ውሳኔያቸውንም ለሚመለከተው አካል የማሳወቅ፣ በህዝበ ውሳኔ ጊዜ የአስተዳደር ወሰን ችግሮ እንዳይከሰቱ ከወዲሁ መስራት እና ህዝቡ የተስማማባቸውን ምልክቶች ቢያንስ በሦስት አማራጮች አዘጋጅቶ ማቅረብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የኮሚቴው አባላት በበኩላቸው የደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልልነት ጥያቄ ህዝቡ ረዘም ላሉ ዓመታት ሲያነሳው የነበረ በመሆኑ በህዝብ ዘንድ ቅሬታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ሂደቱን እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ግጭት ለመፍጠር ከውስጥም ሆነ ከውጪ የሚንቀሳቀሱ አካላት ሊኖሩ ስለሚችሉ የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች ከወዲሁ እንደሚሰሩና በፀጥታ ዘርፉም በኩል ተገቢ ዝግጅት መደረጉንም ነው ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ የሚያመለክተው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.