Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ኢትዮጵያ ድጋፏን ትቀጥላለች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት አተገባበር የክትትልና ግምገማ ኮሚሽን ምክትል ሊቀ-መንበር ሜጀር ጄኔራል ቻርለስ ታይን ጋር ተወያይተዋል፡፡

ምክትል ሊቀ-መንበሩ አቶ ደመቀ ዳግም በመመረጣቸው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በማስተላለፍ፤ የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለማስቆም በተፋላሚዎች መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነትን አተገባበርን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዲረጋገጥ ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን ዘርፈ ብዙ ድጋፎችን በውሳት፤ የተፈረው ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ የተዋሄደ ብሄራዊ ሰራዊት አለመደራጀቱ፣ በጎሳዎች መካከል ግጭቶች መኖር እንዲሁም የፋይናንስ እጥረት ዋነኛ ችግሮች መሆኑን መጥቀሳቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በስምምነቱ መሰረትም በቀጣይ ምርጫ ተደርጎ አዲስ መንግስት ለማዋቀር ጊዜው እየተቃረበ ቢሆንም ህገ-መንግስት ማርቀቅ፣ የምርጫ ተቋም ማደራጀት፣ የፀጥታ ችግሮች፣ ሰው ሰራሽና በተፈጥሮ የተከሰቱ ሰብአዊ ቀውሶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገቢ ሚና አለመጫወት ተጨማሪ ተግዳሮቶች በመሆናቸው፣ የኢጋድ አባል አገሮች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲደርጉ ምክትል ሊቀ-መንበሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ ደመቀ በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያ መልካም ጎረቤት በሆነችው ደቡብ ሱዳን ሰላም ይሰፍን ዘንድ ኢትዮጵያ የበኩሏን ድጋፍ እንደሚታደርግ አረጋግጠው በቀጣይ ኢጋድ በመሪዎች ደረጃ በሚያካሂደው ስብሰባ ላይ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.