Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እያካሄዱ ነው

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በወቅታዊ ሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ላይ በሀዋሳ ከተማ ውይይት እያካሄዱ ነው።

በደቡብ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ አለም ዘርፍ ሀላፊ አቶ አክሊሉ ታደሰ በውይይት መድረኩ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፥ በክልሉ በየደረጃው ያለው አመራር በሀገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች የጋራ አቋም በመያዝ የተጀመረውን ለውጥ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

አመራሩ የሀሳብ እና የተግባር አንድነቱን በማጠናከር ለተሸለ ለውጥ መስራት እንደሚገባም አብራርተዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የለውጥ ምዕራፎችን መሻገር የተቻለ ቢሆንም፤ ለውጡን ምክንያት በማድረግም ሀገር የማፍረስ ተልዕኮን ያነገቡ ሀይሎች በህዝቦች መካከል ልዩነት በመፍጠር የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ጥረት ማድረጋቸውንም አንስተዋል።

“ጥንካሬያችንን በማስቀጠል የስርዓቱ ግብ የሆነውን ብልጽግናን የማረጋገጥ ስራችንን ማስቀጠል ይገባል” ያሉት አቶ አክሊሉ፥ የሀገሪቱን ህብረ ብሄራዊ አንድነት በማስቀጠል ለላቀ ስኬት መስራት ያስፈልጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ባለፉት 28 አመታት አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ህብረተሰቡ ለእንግልት የሚዳረግ እንደነበር የተናገሩት አቶ አክሊሉ፥ በተለይ ሌብነት ዘረፋ የሀብት ብክነት እና መሰል የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መኖራቸውን አስረድተዋል።

ይህንን ተከትሎም ያለፉትን አመታት ችግሮች በሀገራዊ ለውጡ የማረም ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም አብራርተዋል።

በክልል የመደራጀት ጉዳይ አይነኬ እንደነበር ያስታወሱት ሀላፊው ጥያቄውን ለማስተናገድም የነበረው ጫና ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።

የውይይት መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑንም ከደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.