Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ባለፉት 6 ወራት ከ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደቡብ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን ባለፉት 6 ወራት ከ 5 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በበጀት አመቱ ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤት በአጠቃላይ 12 ቢሊየን ብር ግብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በግማሽ ዓመቱ ከ5 ቢሊየን በላይ ብር መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል።

ገቢው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል።

ተቋሙ ከዚህ በፊት የሚታዩ ክፍትቶችን በመለየት በቴክኖሎጂና በአስተሳሰብ አብሮ ሊሄድ በሚችል መልኩ የሰው ሃይል አቅሙን ለማሳደግ ባደረገው ጥናት መሰረት የሰው ሀይል አቅሙን አጎልብቶ ወደ ስራ መግባቱንም አስረድተዋል።

ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ያለው ቀልጣፋና ውጤታማ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመገንባት እና ገቢ በመሰብሰብ መንግስት ለህብረተሰቡ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች እንዲሁም ከህዝብ ለሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የሚያችለውን የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑም ተመላክቷል።

ከግብር ከፋዩ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ተቀብሎ በሕግ አግባብ ምላሽ ለመስጠት ቋሚ የስራ ክፍል እንዲኖር በማድረግ 561 ለሚሆኑ ቅሬታ አቅራቢዎች ምላሽ መሰጠቱን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሕግ የተደነገጉ ግብር የአከፋፈል ስርዓት በመተላለፍ የማጭበርበር፣ ግብር ስወራ፣ ያለ ደረሰኝ ሽያጮችን የሚያከናውኑ ግብር ከፋዮች ላይ ህጋዊና አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.