Fana: At a Speed of Life!

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ለህልውና ዘመቻው የስንቅ ዝግጅት እያከናወነ ነው

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 15 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ለህልውና ዘመቻው የስንቅ ዝግጅት ማከናወኑን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ ገንዘብ በማሰባሰብ ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ፣ ፋኖና ለክተት ጥሪ ዘማቾች ስንቅ በማዘጋጀት ደጀንነታቸውን እያሳዩ ነው፡፡

በስንቅ ዝግጅቱ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ሕይወት ጌታሁን ከዚህ በፊት ደመወዛቸውን እንዳበረከቱ ገልጸዋል፡፡

እኛ የጣይቱ ልጆች ነን የሚሉት ወይዘሮ ሕይወት ወንድሞቻችን በየግንባሩ እየተፋለሙ እኛ ቁጭ ልንል አይገባም፤ ስንቅ ማዘጋጀት፣ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣ ምሽግ ድረስ በመሄድ ማበረታታት ይገባናል ነው ያሉት፡፡

ወይዘሮ ያምሮት እዘዘው በበኩላቸው÷ ከዚህ ቀደም ለህልውና ጦርነቱ የወር ደመወዛቸውን እንደሰጡና አሁንም ከኪሳቸው ብር አውጣጥተው የዳቦ ቆሎ ስንቅ ዝግጅት እያከናወኑ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የሕግ ትምህርት ክፍል አስተማሪ የሆኑት ስለሽ ዋለልኝ በበኩላቸው ደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ በራሱ ተነሳሽነት ግንባር ገብተው ለሚፋለሙት ሠራዊቶቻችን ገንዘብ በማውጣጣት በከፍተኛ መነሳሳት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

መምህር ስለሺ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ከስንቅ ዝግጅት በተጨማሪ ግንባር ገብቶ በመዋጋት፣ ሠራዊቱን በማነቃቃትና በሌሎች ተግባራት የህልውና ትግሉን እያገዘ እንደሚገኝ መጠቆማቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ጦርነት የከፈተ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ወራሪውን ኃይል ለማጥፋት የድርሻውን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡

የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በቀጣይም ግንባር ገብቶ በመዋጋት፤ ለሠራዊቱ ስንቅ የማቅረብና የዘማቾችን ሠብል የመሰብሰብ ሥራን ለማከናወን እቅድ እንዳለውም ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.