Fana: At a Speed of Life!

የድሬዳዋ ከተማ፣ የአፋርና ሐረሪ ክልሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር፣ የአፋርና ሐረሪ ክልሎች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚያስችሉ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፉ።

በድሬዳዋ አስተዳደር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው ግብረኃይል የተለያዩ ውሳኔዎች ማሳለፉን የአስተዳደሩ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ አቶ እዝቅያስ ታፈሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

በዚህም መሰረት፦

ወደ ድሬዳዋ ከተማ የሚገቡም ሆነ የሚወጡ ከፍተኛ እና መለስተኛ ሀገር አቋራጭ
የህዝብ ትራንስፓርት አገልግሎት ከነገ መጋቢት 23 2012 ዓ.ም ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተወስኗል።

ማንኛውም አይነት የድሬዳዋ ከተማ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ባጃጅና ጋሪን ጨምሮ እስከ ሚኒባስ ድረስ ከነገ መጋቢት 23 ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ ተወስኗል።

በየትኛውም የድሬዳዋ አቅጣጫ የሚገኙ የድሬዳዋ መግቢያ በሮች ከነገ ጀምሮ ከእንቅስቃሴ ዝግ መደረጋቸውን ያስታወቀው አስተዳደሩ፥ የእለት መሰረታዊ ፍጆታ እቃዎችን መሰረት ያደረጉ የገበያ ቦታዎችን ሳይጨምር እንደ ታይዋንና አሸዋ የመሠሉ የግብይት ስፍራዎች ከነገ ጀምሮ ዝግ እንዲሆኑ ተወስኗል።

ከፍተኛ የሰው ኃይል ያላቸው ፋብሪካዎች እረፍት በመስጠት እና በሽፍት በማሰራት የሰው ኃይል ቁጥር እንዲቀንሱ ተወሰነ ሲሆን፥ ክልከላው ወደከተማዋ የሚገቡ ነዳጅና እህልን ጨምሮ ሌሎች የፍጆታ እቃዎችንና የሎጂስቲክ እንቅስቃሴዎችን አይመለከትም።

አፋር ክልልም ከዚህ በፊት የተላለፉት ውሳኔዎች እንደተጠበቁ ሆነው በትራንፖርት ዘርፍ ተጨማሪ እገዳዎች ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በክልሉ በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ ባለሦስት እግር ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ መለስተኛና አነስተኛ ተሽከርካሪዎች ከመደበኛ የመጫን አቅማቸው 50 በመቶ ቀንሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ተወስኗል።

ክልሉን አቋርጠው የሚያልፉ ሀገር አቋራጭ የሕዝብና የጭነት ተሽከርካሪዎች በክልሉ ሰው መጫንም ሆነ ማውረድ እንደማይችሉ ካቢኔው ወስኗል።

የሀረሪ ክልል መንግሥትም በተለያዩ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ላይ እገዳዎች ያሳለፈ ሲሆን፥ ማንኛውም ዓይነት የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከዛሬ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ከሌላ ክልል ወደ ክልሉ መግባት እንደማይችልና በክልሉ የከተማ ታክሲ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ማናቸውም ዓይነት ተሽከርካሪዎች አገልግሎት እንዳይሰጡ መታገዳቸውን የክልሉ ካቢኔ ገልጿል።

በክልሉ ውስጥ ከከተማ ወደ ገጠር እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረጉ የትራንስፖርት ጉዞዎች ከዚህ ቀደም በተላለፈው ክልከላ መሠረት ከተፈቀደላቸው የመጫን መጠን በግማሽ ቀንሰው እንዲያጓጉዙ ተወስኗል።

ማንኛውም የግል አውቶሞቢል ወደ ክልሉ ሲገባም ሆነ ሲወጣ እንዲሁም በክልሉ ውስጥ በሚንቀሳቀስበት ወቅት ከሦስት ሰው በላይ መጫን የተከለከለ መሆኑን ተጠቅሷል።

ለኅብረተሰቡ ኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን የሚያመላልሱ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሾፌርና ረዳት ብቻ በመያዝ ወደ ክልሉ መግባትና መውጣት የሚችሉ መሆኑ ተገልጿል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.