Fana: At a Speed of Life!

የጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ታሪክ ዘመኑ በሚጠይቀን የትግል አውድ ላይ ለመድገም በጋራ እንቁም- አቶ ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቀደሙ ጀግኖቻችንን የድል አድራጊነት ታሪክ ዘመኑ በሚጠይቀን የትግል አውድ ላይ ለመድገም ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ፅናት በጋራ ልንቆም ይገባል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ለ81ኛው የአርበኞች ቀን መታሰቢያ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ የአርበኞች ቀንን በልዩ ትኩረት እና ክብደት የምንዘክረው ጀግኖች አርበኞች ለሀገር አንድነት እና ሉዓላዊነት መከበር የከፈሉትን ዋጋ በትውልዱ ዘንድ ተምሳሌታዊ የድል አድራጊነት መንፈስ እንዲጋባ በማሰብ ነው ብለዋል።
ታሪክ በከፍታ እንደሚገልፀው ጀግኖች አርበኞች በእናት ሀገር ላይ የተቃጡ ጥቃቶችን በመመከት እና በጠላት ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ አኩሪ ድሎችን ተቀዳጅተው ነፃና ሉዓላዊት ሀገር ማስረከባቸውን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ጀግኖች አርበኞች ሀገራችንን ከወራሪ ጠላት ለመጠበቅ በዱር በገደል በመዋደቅ እና አኩሪ ገድል በመፈፀም በትውልድ ቅብብሎሽ የድል አድራጊነት ዘላቂ ፈለግ አውርሰው ማለፋቸውንም አመላክተዋል።
በዚህ ረገድ ዘንድሮ ለ81ኛ ጊዜ በኩራት የምንዘክረው “የአርበኞች ቀን” ሀገራችን ያለችበት አሁናዊ ሁኔታ ተከትሎ፤ለትውልዱ የሚቸረው ታሪካዊ ትርጉም በእጅጉ የተለየ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
በዜጎቻችን ላይ የተጋረጡ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን የሚያቀሉ የልማት ውጥኖቻችን በፍጥነት ለማረጋገጥ ከጀመርነው ሁሉአቀፍ ርብርብ አኳያ “የአርበኞች ቀን” የሚያላብሰን ተምሳሌታዊ ትጋት እና ወኔ በልዩነት እና በከፍታ ይታያል ብለዋል።
እንደሃገር የገጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገር ለመጪው ትውልድ ነፃ፣ ሰላማዊ እና የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማውረስ ዳር እስከዳር አንድነታችንን ማጥበቅ እና መጠበቅ ይገባናልም ነው ያሉት።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.