Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ ሰራዊት “በትግራይ ክልል ንጹሃንን ፈጅቷል” በሚል በጁንታው ተላላኪዎች የሚናፈሰው የተቀነባበረ የሃሰት ወሬ ነው -መከላከያ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መከላከያ ሰራዊት “በትግራይ ክልል ንጹሃንን ፈጅቷል ” በሚል በጁንታው ተላላኪዎች የሚናፈሰው የተቀነባበረ የሃሰት ወሬ መሆኑን የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ይህንኑ የፈጠራ ወሬ በሚመለከት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የተለቀቀው ቪድዮም በጁንታው ተላላኪዎች በውሸት ተቀናብሮ ህዝብ ለማደናገር የተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄኔራል መሀመድ ተሰማ ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የመከላከያ ሰራዊቱ ባካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ጽንፈኛውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መደመሰሱን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ የጁንታው ርዝራዦች የሸፋታነትን ባህሪ ለመላበስ በጫካ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በአሳቻ ስፍራ ላይ እየተገኙ በህዝቡ ላይ ዘረፋ፣ እንግልትና ግዲያ እየፈፀሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጁንታው ርዝራዦች ሰላማዊ ሰዎችን በመጨፍጨፍ ሀገርና ህዝብን እየጠበቀ ባለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተፈፀመ ለማስመሰል እየጣሩ መሆኑን አብራርትዋል።

የፅንፈኛ ቡድኑ ተላላኪዎች በጁንታው ታጣቂ ሃይል የተፈፀመውን ግዲያ የምስል ቅንብር በመስራት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የመፈፀመው አስመስለው ማሰራጨታቸውን ሜጀር ጀነራል መሀመድ አስታውስዋል።

የሀገር መከላከያ ሰራዊት በከፍተኛ ስነ ምግባር የተገነባ ህዝባዊ መሰረት ያለው የህዝብ ልጅ በመሆኑ ህዝብን የሚጎዳ ተግባር አይፈፅምም ነው ያሉት።

የህወሃት ጁንታ ዘራፊ ቡድን ጫካ ውስጥ ሆኖ ትርክቶችን በማስተላላፍ በህይወት እንዳለ ለማስመሰል ልዩ ልዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛልም ነው ያሉት።

በውጭ ሃይሎች ተቀባይነትን አግኝተናል እያሉ በማደናገር ወጣቶችን ለእኩይ አላማቸው ለማሰለፍ ያደረጉት ጥረትም አለመሳካቱን አብራርትዋል።

በተለያዩ ቦታዎች መሽጎ የሚንቀሳቀሰው ቀሪ የጁንታው ቡድን የሎጀስቲክ እና ሌሎች መሰረታዊ አቅርቦቶች ስለሌላቸው ህዝቡን በማስፈራራትና በመዝረፍ ህይወታቸውን ለማቆት እየጣሩ መሆኑንም ሜጀር ጀነራል መሀመድ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ጊዜም ቀሪ የጁንታው ርዝራዥ በትግራይ ክልል የህዝብ ተቀባይነት ስለሌለው በዜጎች ላይ የዘረፋና ግዲያ ወንጀሉን ቀጥሏል ብለዋል።

በክልሉ ቀሪ የጁንታውን ርዝራዦች ለማደን በሚደረገው ጥረት ህዝቡ እስካሁን ለሰራዊቱ ያደረገውን ድጋፍ ያደነቁት ሜጀር ጀነራል መሀመድ በቀጣይም እንዲጠናከር ጠይቀዋል።

መከላከያ ሰራዊት ቀሪ ርዝራዦች በማደን ይዞ ለህግ ለማቅረብ ሌት ተቀን እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.