Fana: At a Speed of Life!

የገዳ ስርዓት ጥላቻ ሳይሆን ፍቅር የሚሰበክበት ቦታ ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገዳ ስርዓት ጥላቻ የሚሰበክበት ሳይሆን ፍቅር የሚሰበክበት ቦታ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለፁ።

41ኛው የቦረና ጉሚ ጋዮ ጉባዔ በዛሬው እለት በቦረና ዞን መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው መክፈቻ ላይ የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና የጨፌ ኦሮሚያ አፈጉባዔ ወይዘሮ ሎሚ በዶን ጨምሮ ሌሎችም የክልሉ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የኦሮሞ ህዝብ የአእምሮ ስራ ውጤት የሆነው የገዳ ስርዓት የጀመረበት ጊዜ እና አሁን ዓለማችን ያለችበት ሁኔታ እኩል መሆኑን አስታውቀዋል።

ከ328 ዓመት በፊት የገዳ ስርዓት ሲመሰረት ዓለማችን የት እንደነበረች ይታወቃል ያሉት አቶ ሽመልስ፥ አያት ቅድመ አያቶቻችን የአእምሮ ውጤት የፈጠረው የገዳ ስርዓት የኦሮሞን ህዝብ የሚያኮራ ነው ብለዋል።

በገዳ ስርዓት ላይ በተሰሩ የተለያዩ ስራዎች ገዳን በትምህርት ስርዓት ውስጥ እንዲካተት በማድረግ የመማሪያ መጽሃፍቶች ለትምህርት ቤቶች እንዲከፋፈል መደረጉ ተገልጿል።

ከገዳ ስርዓት በተገኘው የዜግነት አገልግሎትም እንደ ኦሮሚያ ክልል በአንድ ዓመት ውስጥ በርካታ የልማት ስራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

የኦሮሚያ ክልል ከገዳ ስርዓት በመማር ከክልል እስከ ቀበሌ ባሉ አደረጃጀቶች ጠንካራ ስርዓት ለመፍጠር እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

የጠንካራ ስርዓት መኖር ኦሮሞን እና የኦሮሚያ ክልልን ያሻግራል ያሉት ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ ይህንን ደግሞ ከገዳ ስርዓት ነው የምንማረው ብለዋል።

“የገዳ ስርዓት ሁሉም ነገር ነው፤ በገዳ ስርዓት መኖር ይጠበቅብናል” ሲሉም ርእሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በንግግራቸው አክለውም፥ ቦረና ውስጥ በርካታ የልማት ስራዎች ያስፈልጋሉ፤ የግጦሽ መሬት ማካለል፣ ውሃ እና የቦረና ኔትዎርክ እንዲሁም የአውሮፕላን ማረፊያ እና የመንገድ መሰረተ ልማት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ለቦረና ህዝብ ያስተላለፉትን መልእክትም ያቀረቡት አቶ ሽመልስ፥ አዲሱ 2013 ዓ.ም የደስታ፣ የሰላምና የብልፅግና እንዲሆነም ተመኝተዋል።

በዛሬው እለት መካሄድ የጀመረው 41ኛው የቦረና ጉሚ ጋዮ ጉባዔ ለሁለት ሳምንታት ቀጥሎ የሚካሄድ መሆኑን የኦ.ቢ.ኤን ዘገባ ያመለክታል።

በዚህ ጉባዔ ላይ አዳዲስ ህጎች የሚወጡ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም የነበረ መልካም ህጎችም እንዲቀጥሉ፤ ጉድለት ያለባቸውም እንዲስተካከሉ ይደረጋል ተብሏል።

በተጨማሪም በዚህ ጉባዔ ላይ በነበሩ እና ባሉ ችግሮች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም ነው የተገለፀው።

በቦረና ገዳ ስርዓት ባለፉት 8 ዓመታት ያገለገሉ ህጎችን በመገምገም መስተካከል ያለባቸው እንዲስተካከሉ ይደረጋል የተባለ ሲሆን፥ በጉባዔው ላይ የሚተላለፉ ውሳኔዎችም በቦረና ዞን ሙሉ በሙሉ ተፈፃሚ እንደሚደረግም ተነግሯል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.