Fana: At a Speed of Life!

የጉሙሩክ ኮሚሽን የኮሚሽኑ ሰራተኞችንና የፌደራል ፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አዋለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 27፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉሙሩክ ኮሚሽን ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ከ3 ወር በላይ በፈጀ ዘመቻ የኮንትሮባንድ እቃዎች፣ አዘዋዋሪዎችንና ተባባሪዎቻቸውን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የጉሙሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ አዘዋዋሪዎቹ በአዋሽ መቆጣጠሪያ ጣቢያ የፌደራል ፖሊስ ሀላፊ የሻለቃ አዛዥ የሆነ ግለሰብን በጥቅም በመደለልና ከፌደራል ፖሊስ አባላትና እና ከአዋሽ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሁለት ሁለት ሰዎችን መልምሎ እንዲያሰማራ በመመሳጠር የኮንትሮባንድ እቃዎችን በቀላሉ ለማሳለፍ መሞከሩን ተከትሎ በደረሰ ጥቆማ ለ3 ወር ክትትል በማድረግ መጋቢት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የኮንትሮባንድ እቃዎቹ፣ አዘዋዋሪዎቹ እና ተባባሪዎቻቸው ጭምር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም 6 ሚሊየን 196 ሺህ ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ልባሽ ጨርቅና ተስማሚነቱ ያልተረጋገጠ የፊት ክሬም፣ ሦስት የፌደራል ፖሊስ አባላት፣ ዋናው አዘዋዋሪ እና የኮንትሮባንድ እቃውን ሲያጓጉዝ የነበረ አሽከርካሪ ተይዘዋል፡፡

እንዲሁም አንድ የአዋሽ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ሰራተኛ፣ አዘዋዋሪው እንዳይያዝ ሽፋን ሲሰጥ የነበረ አንድ የመተሃራ ፖሊስ አዛዥ በድምሩ ሰባት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡

በጉቦ መልክ ሊሰጥ የነበረ 200 ሺህ ብር መያዙንም አስታውሰዋል፡፡

ኮሚሽነሩ ሀገርና ህዝብ የጣለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ከፍተኛ ዋጋ ለከፈሉ የአዋሽ ጉሙሩክ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት አመራሮችና ሰራተኞች፣ በዘመቻው ለተሳተፉ የፌደራል ፖሊስ ምርመራ ቢሮ እና የወንጀል መከላከል ዘርፍ፣ ስራውን ከመጀመሪያ ጀምሮ በማቀድና በመምራት ለውጤት ላበቁት የጉሙሩክ ህግ ማስከበር ዘርፍና የኢንተለጀንስ አመራሮችና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል፡፡

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.