Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን ገለጹ

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ፣ ቦንጋ እና አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ጥያቄዎች በተለያዩ ሀይሎች ሴራ እንዳይጠመዘዝ አስቀድመው በመስራታቸው የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አስታወቁ።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሃይማኖት እና ብሄር ተኮር ግጭቶች ማዕከል ሆነው ጥቂት የማይባሉ ዩኒቨርሲቲዎችም በተደጋጋሚ ትምህርት ለማቆም ተገደዋል፤ በተማሪዎች ላይም ጉዳት አጋጥሟል።

የግጭት መንስኤዎች የተለያዩ ሲሆን አንዳንዶቹ ከአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ጋር የተያያዙ ናቸው።

የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጴጥሮስ ወልደጊዮርጊስ ግን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ የሚታዩት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ለግድያ የሚያደርሱ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።

አብዛኛዎቹ ተማሪዎች ሰላም ወዳድ መሆናቸውን የሚገልጸው ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማሩን ለማወክ የሞከሩ ጥቂት ተማሪዎች እንዳልተሳካላቸው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ገልፀዋል።

ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተናገደ የሚገኘው የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲም የመማር ማስተማሩ ሂደት በሰላማዊ ሁኔታ ከቀጠለባቸው ዩኒቨርሲቲዎች መካከል ተጠቃሹ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ባወጣው መርሃ ግብር መሰረት የአንደኛ መንፈቅ አመት ትምህርትን ወደማገባደድ መቃረቡን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ኡጁሉ ኦካክ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል።
የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛይም የመማር ማስተማር ሂደቱ በሰላማዊ ሁኔታ መቀጠሉን አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በተለይም ተማሪዎች በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመቅረፍ ካልተቻለም ለማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ተማሪዎችን ተቀብለው ማስተናገድ ከጀመሩ በኋላ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአጭሩ ለመፍታትም ከተማሪዎች ጋር የሰከነ እና የሰለጠነ ውይይት ማድረጋቸውን የአርባምንጭ እና ጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ገልፀዋል።

ለዚህም ተማሪዎች እያንዳንዱ ጥያቄ በሂደት እንደሚፈታ ማመናቸውና አርቆ ተመልካችነታቸው ሰላማዊ ሁኔታው እንዲቀጥል ትልቁን ድርሻ እንደተወጣም ተጠቁሟል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙባቸው አካባቢዎች የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት መሪዎች እና ወጣቶች በሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ መደረጉንም ዩኒቨርሲቲዎቹ የገለጹት።

የዩኒቨርሲቲዎቹ ባለቤት የሆነው ማህበረሰብ ተማሪዎቹን እንደ ራሱ ልጆች ተመልክቶ እንዲጠብቃቸው የተሰራው ስራም ውጤታማ እንደነበር ነው ፕሬዚዳንቶቹ የገለጹት።

ተማሪዎችም በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታዩ አሰቃቂ ተግባራት እንዳይደገሙ በጋራ መስራት አለባቸው፣ ከስሜታዊ ድርጊትም ሊታቀቡ ይገባልም ነው ያሉት።

የብዙሃኑን ሰላም ለመጠበቅ ጥቂት በጥባጮችን አደብ ማስገዛት ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።

በፋሲካው ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.