Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል እና የአፐር ናይል አስተዳደሮች በድንበር አካባቢ የጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል እና በደቡብ ሱዳን የአፐር ናይል አስተዳደሮች በጋራ የድንበር አካባቢ በጸጥታና ሰላም እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ተስማሙ።

የሁለቱ አስተዳደር አመራሮች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት በጋምቤላ ከተማ ተወያይተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉና በደቡብ ሱዳን የአፐር ናይል አስተዳደር ምክትል ገዥ ሚስተር ጀምስ ቶር ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ እንዳሉት÷ የሁለቱ የተወሳኝ አካባቢዎች ወንድማማች ህዝቦች መካከል ያለውን የህዝብ ለህዝብ ፣ ምጣኔ ሀብታዊና ማህበራዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ተቀራርቦ ለመስራት በሚያስችል ውይይት ተደርጓል ።

በተለይም ሁለቱ ተጎራባች አስተዳደሮች በጋራ ድንበር ያለውን የጸጥታ፣ የሰላምና የጤና ስራዎችን ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በድንበር አካባቢ ያለውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር፣ የወንጀለኞችና የኮንትሮባን እንቅስቃሴ ለመግታት በቅንጅት ለመስራት ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በደቡብ ሱዳን የአፐር ናይል አስተዳደር ምክትል ገዥ ሚስተር ጀምስ ቶር በበኩላቸው ኢትዮጵያን ሁለተኛ አገራቸው እንደሆነች ገልጸዋል።

አገራቸው በነበረበት የጸጥታ ችግር ምክንያት በርካታ የደቡብ ሱዳን ዜጎችን ኢትዮጵያ አስጠልላ ድጋፍና ጥበቃ ማድረጓን አስታውሰዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እያበረከተ ያለው  አስተዋጽኦ መቼም የሚዘነጋ አይደለም” ብለዋል።

በሁለቱ ተጎራባች አገራት ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በድንበር አካባቢ የተጀመሩትን የሰላም፣ የጸጥታና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ተቀራርበው ለመስራት የሚስችላቸውን ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.