Fana: At a Speed of Life!

የጋምቤላ ክልል ጥናትና ቅንጅታዊ አሰራርን ታሳቢ ያደረገ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለመተግበር እየሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 3 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የጋምቤላ ክልል ጥናትና ቅንጅታዊ አሰራርን ታሳቢ ያደረገ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

ኢትዮጵያ ካላት ምቹ የእርሻ ኢንቨስትመንት መሬት ውስጥ አብዛኛውን እንደያዘ የሚነገርለት የጋምቤላ ክልል ካለው አቅም አንጻር በዘርፍ ተጠቃሚ እየሆነ አይደለም።

ባለሃብቶች በዘርፉ ተሰማርተው ክልሉን እንዲያለሙ ጥሪ ቢቀርብም በታሰበው ልክ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።

ባለፉት አመታት በእርሻው ኢንቨስትመንት ዘርፍ በርካታ የውጭና የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች ወደ ክልሉ ገብተው ቢንቀሳቀሱም ከቅንጅታዊ አሰራር መጓደል እና ጥናትን ታሳቢ ያላደረገ የመሬት አሰጣጥ ችግር ተያይዞ የታሰበውን ማሳካት አልተቻለም።

ከዚህ ጋር ተያይዞም 301 ባለሃብቶች መሬት ወስደው ሲጠፉ ከዚህ ውስጥ 56ቱ ብቻ ቀርበው ምክንያታቸውን አስረድተዋል።

ለእርሻ ኢንቨስትመንት ከልማት ባንክ ለክልሎች ከተሰጠው 6 ቢሊየን ብር ውስጥም፥ 1 ነጥብ 64 ቢሊየን ብሩ በጋምቤላ ክልል ፈሰስ የተደረገ ነበር።

ለ126 አልሚዎች ከተሰጠው ከዚህ ብድር ውስጥም አብዛኛው ገንዘብ ለታለመት አላማ ያልዋለ እና ግቡን ያልመታ እንደነበር፥ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡመድ ኡጁሉ ተናግረዋል።

በባለሃብቱም ሆነ በመንግስት በኩል የአመለካከት፣ የአሰራር ችግሮች እና ሙስና ዋነኛ የዘርፉ ማነቆ መሆናቸውም ነው የተነሳው።

ክልሉም በእነዚህና መሰል ምክንያቶች ከእርሻ ኢንቨስትመንት ማግኘት የነበረበትን ጥቅም ሳያገኝ መቆየቱን አንስተዋል።

አሁን ላይም ለችግሩ እልባት ለመስጠት የክልሉ ኢንቨስትመንት ቦርድ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በባለሃብቶች ተይዘው ያለሙ መሬቶች ለመንግስት ተመላሽ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን አውስተዋል።

በቀጣይ የነበሩ ችግሮች እንዳይደገሙና ባለሃብቶች በኢንቨስትመንት ህጉ ላይ በተቀመጠው መመሪያ ብቻ እንዲስተናገዱ እና ክልሉም ለአልሚዎች የተሻለ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።፡

በእርሻ ኢንቨስትመንት ላይ ሳዑዲ ስታር የሚባል የውጭ ድርጅት ብቻ የተሰማራ ሲሆን፥ የጤፍ፣ የሰሊጥና የበቆሎ ምርቶች ደግሞ በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች እየተመረቱ ነው ተብሏል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ በየትኛውም ዘርፍ ተሰማርተው መስራት ለሚፈልጉ የውጭም ሆነ የሃገር ውስጥ ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በመግለፅም ለባለሃብቶች ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.