Fana: At a Speed of Life!

የጋሞ አባቶችና ወጣቶች የአብሮነትና የሰላም ጉዞ ሊያደርጉ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በእርጥብ ሳራቸው ሰላምን ያወጁ የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች የአብሮነትና የሰላም ጉዞ ሊያካሂዱ ነው።

ጉዞው ከጥር 6 እስከ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም የሚደረግ ሲሆን፥ ከአርባ ምንጭ በመነሳት የተለያዩ ከተሞችን በማቋረጥ እስከ ጎንደር ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

በጉዞው አባቶች የአካባቢያቸውን ሰላም እንዴት እንዳስጠበቁ ተሞክሮዎቻቸውን ለሌሎች የሚያካፍሉ ሲሆን፥ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የሰላም ተምሳሌትነትም ለሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተሞክሮነት ይቀርባል ተብሏል።

አባቶች በጉዞው የተለያዩ ከተሞችን የሚያቋርጡ ሲሆን፥ በሚያርፉባቸው ከተሞችም ስለሰላምና አንድነት ይመካከራሉ።

እንዲሁም ተማሪዎችን ስለአቃፊነት፣ ስለ ሰላምና አንድነት እንደሚመክሩም ከጋሞ ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የሰላም ተጓዠ የሆኑት የጋሞ አባቶች እና ወጣቶች በአዲስ አበባ በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተገኝተው የአንድነት ፓርክን ይጎበኛሉ።

የጉዞው መዳረሻ በሆነችው ታሪካዊቷ የጎንደር ከተማም ከከተራ በዓል ጀምረው እስከ ጥር 14 ቀን 2012 ዓ.ም ለአራት ቀናት ይቆያሉም ነው የተባለው።

የአብሮነትና የሰላም ጉዞውን ህብረ መንጎል ሚዲያና ኦሞቲክ ጀኔራል ጠቅላላ ንግድ ድርጅት በጋራ ያዘጋጁት ሲሆን፥ የጉዞውን አላማ በመደገፍ የሰላም ሚኒስቴር፣ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዲሁም የደቡብ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮዎች ለአዘጋጆች የድጋፍ ደብዳቤ ሰጥተዋቸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.